ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የህዝቡን ጠንካራ አጋርነት ያረጋገጡ ናቸው…. ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የህዝቡን ጠንካራ አጋርነት ያረጋገጡ ናቸው…. ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2013(ኢዜአ) ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የህዝቡን ጠንካራ አጋርነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ 18 የግልና የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማትና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነታቸውን ለማሳየት የ205 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ድጋፉ የአገር ኩራት ለሆነው ሠራዊት ለማመስገን፣ ለማበረታታት እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ይሁንልን ብለዋል፡፡
በድጋፍ መርሃ ገብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባዋ አዳነች እንደገለጹት፣ ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የህዝቡን ጠንካራ አጋርነት ያረጋገጠ ነው።
ሠራዊቱም ይህንን ሞራል ሰንቆ ወደ ፊትም የአገሪቱን ሰላምና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ አምናለሁ ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ፊትም በሚያደርጋቸው ተጋድሎዎች የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የባንኮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ድህነትንና ጠላትን መዋጋት ሲገባት በተፈፀመባት የውስጥ ክህደት ተገዳ ወደ ሀግ ማስከበር ዘመቻ መግባቷን አስታውሰዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል የኑስ ሙሉ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ብሎም በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች እስካሁን ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የህወሓት ጁንታ አሰቃቂ ጥቃት ያደረሰው በመከላከያ ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ድጋፉን የኢትዮጵያ ባንኮች ፕሬዚዳንት አቢ ሳኖ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ያስረከቡ ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባዋም ለአገር መከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል የኑስ ሙሉ አስረክበዋል።