የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በሚቀጥለው ሳምንት የመድረክ ቴአትሮችን ለተመልካች ማቅረብ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በሚቀጥለው ሳምንት የመድረክ ቴአትሮችን ለተመልካች ማቅረብ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ ህዳር 30/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የኮቪድ መከላከል መመሪያን ተግባራዊ ባደረገ መልኩ በሚቀጥለው ሳምንት የመድረክ ቴአትሮችን ለተመልካች ማቅረብ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ኮቪድ 19 ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎችን በመተግበር መድረኩን ለተመልካቾች ክፍት ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትር ክፍል ዳይሬክተር ደስታ አስረስ ገልጸዋል።
ቴአትር ቤቱ በአንድ ጊዜ 1 ሺህ 200 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም አሁን ላይ በአንድ ጊዜ 300 ተመልካቾች ብቻ ይስተናገዳሉ ነው ያሉት።
ተመልካቾች ወደ ቴአትር ቤት ሲመጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግ፣ ሳኒታይዘር በመጠቀም እና ተራርቆ በመቀመጥ እንዲመለከቱ ይገደዳሉ ብለዋል።
የመድረክ ትወና አቅራቢዎችም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግና ከንክኪ በመራቅ ዝግጅታቸውን ለታዳሚ እነደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
ለቴአትር ሥራ የሚውሉ ቁሶችም ቴአትሩ ከመጀመሩ በፊት በሳኒታይዘር ይፀዳሉ ብለዋል።
የቴአትር መጀመር በኮቪድ ምከንያት የተቀዛቀዘውን ባለሙያ ወደ ስራ የሚያስገባ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከታህሣሥ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቴአትር ቤቱ ለተመልካች ክፈት ሆኖ በሳምንት ሶስት ቴአትሮችን ለማሳየት ዝግጅት መደረጉንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።