ክፍለ ከተማው ከ145 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ክፍለ ከተማው ከ145 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ አደረገ
ህዳር 30/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ለአንድ ሣምንት በወሰደው እርምጃ በወረራ የተያዘ ከ145 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስመለሱን አስታወቀ።
ክፍለ ከተማው ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊው መግለጫ በሦስት ምዕራፎች የተከፈለ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ እንደገለጹት የተወሰደው ሰፊ የሕግ ማስከበር እርምጃ ስኬታማ ነበር።
እንደ እርሳቸው ገለጻ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክፍለ ከተማው ከፍተኛ የመሬት ወረራ ተፈጽሟል።
የከተማ አስተዳደሩም ሕገወጥ የመሬት ወረራን አስመልክቶ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልፀዋል።
"በጥናቱ መሰረት በክፍለ ከተማው በተለዩ 60 አካባቢዎች በተወሰደው እርምጃ በአንድ ሣምንት ጊዜ ብቻ ከ145 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከሕገወጦች በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ ማስገባት ተችሏል" ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር በተወሰደው እርምጃ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ የተደረገው 500 ካሬ ሜትርና ከዛ በላይ የሆኑ ሕገወጥ ይዞታዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ጥናቱን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በክፍለ ከተማው በ17 የእምነት ተቋማት በልማትና በወረራ የተያዙ ቦታዎችን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተያያዘ ዜና በሕገወጥ የንግድ ሥራ ተሰማርተው የተገኙ 3 ሺህ 800 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
የሕግ ማስከበር ሥራውን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ አስቀድሞ የማስገንዘብ ሥራ በመሰራቱ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ያልተገቡ ሁከቶች ሳይፈጠሩ በሠላማዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ነጻነት ኅብረተሰቡ በሕግ ማስከበር ሂደቱ ላሳየው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።