መንግስት በሕዳሴ ግድብ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በፍጥነት ማስተካከሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲጨምር አድርጓል ... ዶ/ር አረጋዊ በርሄ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በሕዳሴ ግድብ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በፍጥነት ማስተካከሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲጨምር አድርጓል ... ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2013 (ኢዜአ) መንግስት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሕዝቡን እምነት የሚሸረሽሩ አሰራሮችን በፍጥነት ማስተካከል መቻሉ ሕዝባዊ ተሳትፎው እንዲጨምር ማድረጉን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት በ15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለ ልዩነት በተባባረ ክንድ ለግድቡ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ቀጥለዋል ነው ያሉት።
እስካሁንም ባለው ሂደትም ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ከገንዘብ በተጨማሪም በጉልበትና በእውቀት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚቃጡ ዲፕሎማሲያዊ ጥቃቶችን በመመከት ረገድ አኩሪ ተግባር ማከናወናቸውንም ዶክተር አረጋዊ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነት በደመቀ ሕብረብሔራዊ ክንዳቸው ወራሪን ጠላት እንደመከቱ ሁሉ በግድቡ ላይም አስደናቂ ገድል እየሰሩ መሆኑን ተናግረው፤ ይህም ብዝሃነት ለኢትዮጵያ ጸጋ መሆኑን እንደሚያሳይ ነው የገለጹት።
መንግስት በለውጡ ዋዜማ በግድቡ ላይ የሕዝቡን እምነት የሚሸረሽሩ አሰራሮችን ፈጥኖ ማስተካካል መቻሉ ደግሞ ለግድቡ የሚደረገውን ሕዝባዊ ተሳትፎ እንደጨመረው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ሐምሌ 2012 ዓ.ም የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መከናወኑም ለሕዝባዊ ተሳትፎ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን አንስተዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ያለ ምንም ልዩነት ለግድቡ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ግድቡ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።