አስደማሚው የመከላከያ ሠራዊታችን ገድል

በጥላሁን አያሌው(ኢዜአ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉኣላዊነት ከማስከበር አልፎ የጎረቤት እና የሌሎች ወዳጅ አገራትን ሰላም የማስከበር ተልእኮውን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ በመልካም ምግባሩ የተመሰከረለት ነው። የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ከተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመተባበር ተልእኮውን እየተወጣ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ሰራዊቱ የስትራቴጂክ መመሪያው አድርጎ ሲመራባቸው የነበሩ ሰነዶች ከህገ መንግስቱ ጋር እንደሚቃረኑና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ላይ የተመሰረቱ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት ስትራቴጂ ሰነድ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን አስመልክቶ ለከፍተኛ የመከላከያ ኃይሉ መኮንኖችና ኃላፊዎች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ሰነዱ ከህገ መንግስት ድንጋጌዎች አንፃር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነቶች እንዳሉት ገልጸው ነበር። የመከላከያ ሠራዊት የቀድሞው የስትራቴጂ ሰነድ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 87/1/3 እና 5 ካለው ሃሳብ ጋር ይቃረናል። በዚህ የህገ መንግስት ክፍል ላይ የመከላከያ ሠራዊቱ በማንኛውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዥ ይሆናል ይላል፤ ነገር ግን በቀድሞው ሰነድ ላይ "እኛ የምንገነባው የመከላከያ ሃይል የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ዘብ ነው ብለን በግልጽና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው" በሚል ተገልጿል። ይህም ህገ መንግስቱ ከሚያስበው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ጋር የሚቃረን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሰነዱ "የሠራዊቱ ዓላማ የሥርዓቱን ደህንነት መጠበቅና መከላከል ነው፤ ይህም ለአንድ ፓርቲ ዘብ በመሆን መልክ ሊገለጽ ይችላል" በማለት የሚያብራራ ሲሆን ህገ መንግስቱ ግን ለአንድ ፓርቲ ዘብ የመቆም እይታ የለውም። ሰነዱ ላይ “ሠራዊታችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አመራር ያለውና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ይሆናል" በሚል የተገለጸ ሲሆንበህገ መንግስቱ አንቀጽ 87/1 ላይ "የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ የጠበቀ ይሆናል" በሚል በግልጽ ተደንግጓል።

ብርጋዴር ጄኔራል መስፍን ሃይሌ በቅርቡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የመከላከያ ሰራዊቱ አደረጃጀት በተመለከተ ሲገልጹ “ህወሓት ፈጥሮት የነበረው የሠራዊት አደረጃጀት የፖለቲካ ውሳኔ እና ተጽእኖ የነበረበት የጦር አደረጃጀት ነው። በዚህ ውስጥ በመሰረቱ ትልቁን ድርሻ ይዞ አመራር ይሰጥ የነበረው የህወሓት ቡድን ነው። ይህ የታወቀ ነገር ነው።… ግን ህይወት ማስቀጠል የግድ ስለሆነ ነው እንጂ አንዳንድ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት ልክ ለሌላ ሀገር ተቀጥረው እንደሚሰሩ አድርገው ነበር ራሳቸውን የሚያዩት” ሲሉ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀትና የብሔር ስብጥር ሲፈተሽ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ባለአራት ኮከብ ጄኔራሎች 60 በመቶው ከትግራይ ክልል ሲሆኑ ከሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች በሙሉ 40 በመቶ ነበሩ። ሌተናል ጄኔራሎች 50 በመቶ፣ ሜጀር ጄኔራሎች 45 በመቶ፣ ብርጋዴር ጄኔራሎች 40 በመቶ፣ ኮሎኔሎች 58 በመቶ ሌተናል ኮሎኔሎች 66 በመቶ፣ ሻለቃዎች 53 በመቶ ከትግራይ ክልል ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ያለው በአማካይ ሲታይ 55 በመቶው ከትግራይ ክልል መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ የህወሃት ጁንታ ቡድን ያዋቀረው የቀድሞው የሠራዊቱ አደረጃጀት አሁን ብቻ ሳይሆን በሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታት መቀየር እንዳይቻል ተደርጎ የተዋቀረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።      

ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በተደረገው ሪፎርም የመከላከያ ሠራዊቱን አደረጃጀት ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። በአዲሱ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው ሠራዊቱ ለህገመንግስቱ ተገዢ የሆነና ለህዝብና ለአገር ዘብ የቆመ ነው። በዚሁ ሰነድ ላይ እንደተብራራው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዋና ዓላማ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የፀና፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት፣ የሀገረ መንግስቱ እና የሀገረ መንግስቱን ግዛታዊ ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝብ ደህንነት ከማንኛውም ዓይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት መከላከል ነው። የመከላከያ ሰራዊቱ ለፓርቲ፣ ለብሔርና ለቡድን የወገነ ሳይሆን አገራዊ ሉዓላዊነትን መሠረት አድርጎ በህገመንግስቱ የሚመራ ሆኖ አገራዊ ቀጣይነትን የማረጋገጥ ተልእኮ ተሰጥቶታል። በአዲሱ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው ሠራዊቱ የሕዝቦችን ሉዓላዊነት እና የሉዓላዊነታቸው መገለጫ የሆነውን ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን ከወራሪዎች፣ ከአመጸኞች እና ጉልበትን ከሚጠቀሙ ማናቸውም ኃይሎች መከላከል የመጨረሻው ተልዕኮው ነው። ጉልበትን መሰረት ያደረጉ ውጫዊና ውስጣዊ የሉዓላዊነት እና የሕገ መንግስት ጥሰቶች የመከላከል የመጨረሻ ጫፍ የመከላከያ ሠራዊቱ ነው።

ከሀገራዊ የሪፎርም አጀንዳ ያፈነገጠው የጁንታው ቡድን ሀገርን የማተራመስ አጀንዳ ማራመድ ከጀመረ ሁለት ዓመታት አልፏል። ይህ አጥፊ ቡድን “እኔ ያልመራኋት ሀገር ትበተናለች” በማለት በየጊዜው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የእርስ በርስ ትርምስ እንዲፈጠር አድርጓል። ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ብቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሰው ህይወት የቀጠፉና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ያስከተሉ 113 ትላልቅ ግጭቶች አጋጥመዋል። በእነዚህ ጊዜያት የመንግስትን ትኩረት የሚፈታተኑ በእያንዳንዱ ሳምንት ውስጥ በተቀናጀ መንገድ የተሰሩ የጦርነት ድግሶች ነበሩ። የጁንታው ቡድን በያዝነው መስከረም 2013 ዓ.ም መንግስትን ለማስወገድ በተደራጀ መንገድ ሲሰራ እንደነበረ የቡድኑ አባላት በይፋ ተናግረዋል። 

የጁንታው ቡድን አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ባስተላለፉት መልእክት “ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል አይኖርም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል አይኖርም፣ የተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባል አይኖርም፤ ለዚህ ነው መንግስት ያከትምለታል የምንለው” ሲሉ የጁንታውን ምኞት ግልጽ አድርገዋል። አጥፊው ቡድን በተደጋጋሚ “መከላከያውና የጸጥታ ኃይሉ ለመንግስት አይታዘዝም፣ ሀገሪቱ መንግስት አልባ ትሆናለች” የሚሉ ዘመቻዎችንም ከፍቶ እንደነበር ይታወሳል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በውድቅት ሌሊት ማንም ባልገመተው ሁኔታ የጁንታው ቡድን ባደራጃቸው የክልሉ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ከባድ ጭፍጨፋ ተፈጸመ። የሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት የትግራይን ህዝብ ከጥቃት ለመከላከል ከ20 ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ምሽግ ውስጥ ኖሯል። ይሁን እንጂ ውለታቸው ግድያና ጭፍጨፋ ሆነ። ከሀዲዎቹ ሀገራቸውን ወጉ። ይህ ድርጊት በአስነዋሪነቱ ብዙዎችን አነጋግሯል። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ድርጊቱ “በታመነ ጓደኛ ወይም ወገን” የተፈጸመ ሀገርን ለጥቃት አጋልጦ የሰጠ ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ይገልጹታል። 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በዚሁ ዙሪያ ለፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የህወሃት ጁንታ ቡድን በዘረጋው መረብ አማካኝነት ወታደራዊ መገናኛዎችን በመበጣጠስ፣ ስልክና መብራት በማጥፋት በየቦታው ያለ የሠራዊቱ አባላት እርስ በርስ እንዳይገናኝ አድርገውታል። ሠራዊቱን በሚሊሻ በመክበብ እምቢ ያለውን ቄስና ሽማግሌ በመላክ እጅ እንዲሰጥ እየጠየቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ተፈጽሞበታል። የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ “መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመን መሳሪያውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረናል” ሲል በይፋ ተናግሯል። የህወሃት ቡድን አባል የሆኑት አቶ ሴኩ ቱሬ ጌታቸው በክልሉ ሚዲያ ላይ “የሰሜን እዝን በ45 ደቂቃ መብረቃዊ ምት መትተን ተቆጣጠርነው" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። የህወሃት ጁንታ ገና ከመነሻው የዲጂታል ወያኔ አራጋቢዎችን በማሰማራት መከላከያ ሰራዊታችን ውስጥ መከፋፋል እንዳለ፣ ወይም አለመደማማጥ እንደሚታይ በማስመሰል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በስፋት ሲያሰራጭ ቆይቷል።

የህግ ማስከበርና የሉዓላዊነት ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ የቀደመ የሀሰት ትርክታቸውን በማጠናከር በሀገር ውስጥና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የጁንታው ቡድን ቅጥረኞች ዘመቻው በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጦርነት እንደሆነ ሲያሰራጩ ከርመዋል። የጁንታው መሪዎች በትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን እየወጡ "የሰሜን እዝ ከእኛ ጋር በመተባበር እየተዋጋ  ነው" የሚል መረጃም አሰራጭተዋል።  እውነታው ግን በተቃራኒው ነበር።

የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ያደረሰው እጅግ ዘግናኝ ጥቃት ዓላማው በመጀመሪያ የሰሜን እዝ መምታት በማግስቱ ደግሞ ጎንደርና ወልዲያን መቆጣጠር እንዲሁም አዲስ አበባና በክልል ከተሞች ጭምር በተላላኪዎች በኩል የተለያዩ ፍንዳታዎችን በማድረስ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ የመንግስትን ስልጣን መቆጣጠር እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ የጁንታውን ቡድን ዓላማ ለማክሸፍና ህግ ለማስከበር የሚያስችለውን አደረጃጀት በፍጥነት በመመስረት ከመከላከል አልፎ ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል። የደረሰበትን ጥቃት ተቋቁሞ የጁንታውን ቡድን ለህግ ለማቅረብ የፈጠረበት ቁጭትና የወሰደው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነበር። የመጀመሪያ የሰራዊቱ ተልእኮ የነበረው ጎንደርና ወልዲያ በጁንታው ቁጥጥር ስር እንዳይውል የመከላከል ስራ መስራት ነበር።

ፓርላማው ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ሁሉም የታጠቀ ሃይል በአንድ ኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን ተደርጎ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ከጁንታው ቡድን ጋር ግንኙነት የፈጠረውን ኦነግ ሸኔን የማጥቃት ተልእኮ ወስዶ እየሰራ ነው። የአማራ እና የአፋር ክልሎች ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ህግ ማስከበሩ በተጀመረበት ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው ድንበር አካባቢዎች የመከላከል እርምጃ ከመውሰዳቸውም ባሻገር የጁንታው ቡድን ወደ ጎንደር እና ወልዲያ ለመግባት የነበረውን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ አክሽፈዋል። የቤንሻንጉል ልዩ ሃይልና ፖሊስ ቤንሻንጉል አካባቢ ያለው የጸጥታ ማሰከበር ተልእኮ ተሰጥቷቸው በብቃት ፈጽመዋል። የፌዴራል ፖሊስ አዲስ አበባ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት የነበራቸውን የጁንታው ቡድን ተልእኮ የያዙትን አካላት ቀን ከሌሊት በመከታተል ጥቃት እንዳይፈጸም ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። ለእነዚህ ሁሉ ክብር ያስፈልጋቸዋል። ሠራዊቱ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የመሸገባቸውን ምሽጎችን አፈራርሶ የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ድል ለመንሳት ያደረገው ገድል ታሪክ አይረሳውም።

የመከላከያ ሠራዊቱ የተከተለው አካሄድ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የከተማ ውጊያ ማስቀረት፣ ሳያውቁ በዚህ ድርጊት ላይ የተቀላቀሉ ሃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ እድል እንዲያገኙ ማድረግ፣ የጠላትን አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ በማድረግ የህግ ማስከበሩ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማስቻል ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም የተሳካ ስራ ተሰርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በጁንታው ጥቃት ወደ ኤርትራ ያፈገፈገውን ጦር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ሶስት ጄኔራሎችን ማለትም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጄኔራል ባጫ ደበሌ እና ጄኔራል  ጌታቸው ጉዲና በመያዝ ኤርትራ በመጓዝ የሰራዊቱን አባላት ጎብኝተዋል። በዚህ ወቅት ጄኔራል አበባው ታደሰ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አይቶ  "ከሠራዊቱ ጋር እየተዋጋሁ በእግሬ እገባለሁ እንጂ አልመለስም" በማለት በቁጭት ሰራዊቱን ለመምራት ተልእኮ ወስደዋል። በተመሳሳይ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና  እና ጄኔራል ባጫ ደበሌ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሠራዊቱን ለመምራት  ዝግጁ ሆኑ። ወደ ኤርትራ ያፈገፈጉት የሠራዊቱ አባላትም ከፍተኛ ወኔና ቁጭት ፈጠረባቸው። እነዚህ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ብዙዎቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ትጥቃቸውን ይዘው ማርከው የገቡ ነበሩና “በፍጥነት ይህንን ጁንታ ወደ ህግ እናቅርብ፤ እዚህ እንዳታቆዩን” የሚል ወኔ ሰንቀው ነው ወደ መልሶ ማጥቃት መግባታቸው የተነገረው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጦሩን በብቃት በመምራት ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን የጦር መሪዎች ሳተናው፣ ልበ ቆራጡ፣ ትንታጉ፣ ነበልባሉ፣ ግስላው፣ ወታደራዊ ሊቁ፣ ነጎድጓዱ፣ አይበገሬው፣ በሀገሩ የማይደራደረው፣ አነፍናፊውና የጠላትን ኮቴ የሚከታተለው፣ ካርታን እንደምድር የሚያነበው፣ ሎጅስቲክስን የሚያሳልጠው፣ የሰው ሃይልን በከፍተኛ ደረጃ የሚያመጋግበው፣ አርድ አንቀጥቅጡ፣ ንስሩና መሰል ቃላትን በመጠቀም ጀግንነታቸውን አወድሰዋል።

ጄኔራል በላይ እና ጄኔራል መሰለ በጎንደርና በሁመራ በኩል የመጀመሪያውን የመከላከል ሥራና ሁመራን የመቆጣጠር ተልእኮ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ሆነው መርተዋል። ጄኔራል አበባው በምዕራብ ግንባር በኩል ሠራዊቱን አደራጅቶ ባድመና ዙሪያው ያሉትንና ሽራሮን የመቆጣጠር ተልዕኮ በመውሰድ በብቃት መርቷል። ጀኔራል አበባው ገመሃሎም፣ ባድመ  የመሳሰሉትን ምሽጎች ይዞ ሽራሮን እንዲቆጣጠር ተልእኮ ተሰጥቶታል። ጄኔራል በላይና ጄኔራል መሰለ ሁመራን ከያዙ በኋላ አዲጎሹን ይዘው ተከዜን ተሻገረው ሽራሮ ላይ ከጄኔራል አበባው ሃይል ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ። ይህ ሃይል ተደምሮ ነው ሽሬንና አክሱምን በፍጥነት መቆጣጠር የቻለው። ጄኔራል ባጫ ደበሌ በራያ ግንባር ወደ እንጥጮና አድዋ የሚወሰደውን መስመር በመምራት አኩሪ ስራ ሰርተዋል። ጄኔራል ጌታቸው በዛላንበሳ በኩል ሠራዊቱን አደራጅቶ በከፍተኛ ጀግንነትና ቆራጥነት ዛላምበሳንና አዲግራትን እንዲቆጣጠር የተሰጠውን ተልዕኮ አሳክቷል። በምስራቅ በኩል ከባድ መሳሪያዎችን በማደራጀት የመራው ወታደራዊ ሊቁ ጄኔራል አለምሸት፣ ጄኔራል ሰለሞን፣ ጄኔራል ዘውዱ በጋራ በመምራት አኩሪ ገድል ፈጽመዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ሁለት የማዘዣ ጣቢያዎችን በመያዝ 24 ሰዓት ያለእረፍት የሚሰሩ ጀግኖች ጄኔራሎችን በመያዝ በኮማንድ ፖስት አጠቃላይ ውጊያውን መርተዋል። ጄኔራል ዮሃንስ፣ ጄኔራል አስራት፣ ጄኔራል ተስፋዬ፣ ጄኔራል አብዱራህማን፣ ጄኔራል ሃጫሉ፣ ጄኔራል ሃሰንና ሌሎችም በአንድ ኮማንድ ፖስት ስር ሆነው በሁለት ማዘዣ ጣቢያዎች ቀንና ማታ ውጊያውን በብቃት መርተዋል።  

አርድ አንቀጥቅጡ የአየር ሃይል አዛዥ ጄኔራል ይልማ በከፍተኛ ደረጃ ጀግኖች ተዋጊዎችን በመያዝ በታሰበው ልክ ጦርነቱ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ  ተጋድሎ ፈጽመዋል። ጄኔራል ሹማና ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ልዩ ሃይል በማደራጀት በዓለም ላይ ሊገኝ የማይችል ጀግንነት ፈጽመዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መሠረት የጁንታው ሃይል በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከሽራሮ መቀሌ ከተማ ለመግባት 15 ዓመታት ፈጅቶበታል። ይህ ሠራዊት ግን በአስራ አምስት ቀን ገብቷል። ሁኔታው በፊልም ካልሆነ በስተቀር ለማስረዳትና ለማብራራት ይከብዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት በህግ ማስከበሩ የሠራዊቱ የልዩ ሀይል አባላት ገድል እጅግ አስገራሚ ነበር። ይህ ሃይል መቀሌ ላይ አንድም ሰው ሳይሞት ከተማዋን ለመቆጣጠር ያደረገው ጀግንነት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። በሁመራ ላይ የነበረው ምሽግ ይህ ልዩ ሃይል አንድ ሰው ሰውቶ ብርጌድ አፍርሷል። በምስራቅ እዝ የሄደው ልዩ ሃይል ፊት ለፊት ያየውን ጠላት አልዋጋም ብሎ ሰርስሮ ገብቶ ውጊያው የገጠመው ከአዛዦቹ ጋር ነው። ጥይት ጨርሶ እንኳ በእጁ ተናንቆ ከጠላት መሳሪያ የቀማ ጀግና ነው። የ7ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጄኔራል ግርማ ክበበው ክፍለ ጦሩ እየተዋጋ "እስከመጨረሻው እሞታለሁ እንጂ መሳሪያዬን አልሰጥም" ብሎ ሃይሉን ይዞ ሙሉ ትጥቁን ይዞ፤ መሸከም ያልቻለውን አቃጥሎ ወደ ኤርትራ በመግባት ጀግንነቱን አሳይቷል። ወደ ኤርትራ የወጣው መድፍ እና ታንክን ጨምሮ የተደራጀ ትጥቅና ሃይል በመያዝ ነበር። በተመሳሳይ የ5ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሙሉዓለም መሸሻ በሁመራ አካባቢ የወገን ጦር እስከሚደርስለት ድረስ እየተዋጋ አንድም ትጥቅ ሳያስወስድ የቆየ ጀግና ነው። በባድመ በኩል ደግሞ የ8ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጄኔራል ናስር አባዲጋ ሙሉ ክፍለጦር  ይዞ  በብቃት ተዋግቶ በድል ተወጥቷል። በኋላም ሽራሮን የተቆጣጠረው ይኸው ክፍለ ጦር ነው። እንደእነዚህ ዓይነት ለህይወታቸው ቅንጣት ያህል የማይሳሱ ጀገኖች ኢትዮጵያ ወልዳለች።ይህ ባይሆን ኖሮ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገሪቱን ሊበታትናት ይችል እንደነበር ጥርጥር የለውም።   

ሠራዊቱ በሁሉም ግንባሮች ያሳየው ገድል እጅግ የሚደነቅ ነበር። ሁሉንም አካባቢዎች በፍጥነት ነፃ በማውጣት ወደ መቀሌ ሲገሰግስ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በንፁሃን ዜጎች ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ብሎም ተገደው ወደ ጦርነቱ የገቡ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላትን ለማዳን በማሰብ በርካታ የጥንቃቄ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጁንታው ቡድን እጁን እንዲሰጥ የ72 ሰዓታት ጊዜ መሰጠቱ ነው። ሠራዊቱ በንፁሃን ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ራሱን የቻለ ልዩ ዕቅድ አዘጋጅቶ ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ ተልእኮውን ተወጥቷል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሀገርን ሉአላዊነት የተዳፈረና ለጠላት አጋልጦ መስጠት በመሆኑ ሠራዊቱ ህግን የማስከበርና የሀገርን ሉአላዊነት የመጠበቅ ተልእኮውን በብቃት አሳክቷል። ሠራዊቱ ወትሮም እንደተለመደው በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ሥራ ድል በመቀዳጀት ታሪካዊ ጀብድ መፈጸም ችሏል። ምንም እንኳን በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ስሜታዊ የሚያደርግ ቢሆንም የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ በህዝቡ ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይፈጸም ጥበብ በተሞላበት አኳኋን ተልዕኮውን በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል። በዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህዝብ የተገነባ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት የቆመና በመልካም ስነምግባር የታነፀ መሆኑን አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም