ቀጥታ፡

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ልዑካን ቡድን በጂዳ ሼሜሲ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጎበኘ

አዲስ አበባ ህደር 30/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ ሼሜሲ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጎብኝቷል።

ቡድኑ የዜጎቹን አያያዝ አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋርም ተወያይቷል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ የተመራው የልዑካን ቡድን በጂዳ ሼሜሲ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ዜጎችን ትናንት ሲጎበኝ የምግብ፣ የጤና አጠባበቅና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ከጉብኝቱ በኋላ የልዑካን ቡድኑ በማዕከሉ ያሉና የተመላሽ ዜጎችን መብትና ደህንነት በማስጠበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር መወያየቱን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ውይይቱ የተካሄደው ከማቆያ ማዕከሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም ከኢሚግሬሽንና ከአየር መንገድ ተወካዮች ጋር ነው።

ጉብኝቱንና ውይይቱን መነሻ አድርጎ ለመንግስት የሚቀርብ ምክረ ሃሳብ እንደሚዘጋጅና በቀጣይ ቀናት ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ኤጀንሲው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ የተመራው የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ በዜጎች መብትና ደህንነት ማስጠበቅ፣ በዳያስፖራውና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያያት ሕዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ሳዑዲ ማቅናቱ ይታወቃል።

የልዑካን ቡድኑ ከጥቂት ቀናት በፊት በጂዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶችና በጂዳና አካባቢዋ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር መወያየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም