ቀጥታ፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ለዘገባ የተሰማሩ ጋዜጠኞች የሙያውን ስነ ምግባር ጠብቀው ሰርተዋል-- ብሮድካስት ባለስልጣን

አዲስ አበባ ህደር 30/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በተከናወነው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለዘገባ የተሰማሩ ባለሙያዎች የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር አክብረው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ሚዲያ ተቋማት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በዘገባ ለተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዕውቅና እና ውይይት  አካሂዷል።

በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙን ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በህግ ማስከበር ስራው ላይ የነበሩት ዘገባዎች የሙያውን ስነ ምግባር የተከተሉ ነበሩ ብለዋል።

በስፍራው ተሰማርተው የዘገቡ ጋዜጠኞች ያሳዩት ሙያዊ ብቃት ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት በቀጣይም  በምሳሌነት የሚጠቀስ ይሆናል ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው "ባለሙያዎች መረጃ በማድረስና ከወታደሩ እኩል ፈተናውን በመጋፈጥ ለተሳተፉበት ሥራ ዕውቅና እና ምስጋና መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የፅንፈኛው የህወሓት ከሃዲ ቡድን ጥቃት ከሠራዊቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊነትና የአገር ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት መሆኑን አንስተዋል።

የችግሩን መጠን ከማሳየት በተጨማሪ በቀጣይ ኢትዮጵያዊነትና አገራዊ አንድነት ዳግም በአዲስ ተስፋ እንዲያንሰራራ የመገናኛ ብዙን ተቋማት ትልቅ ኃላፊነትና የቤት ሥራ እንደተጣለባቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው ኢትዮጵያ "የመከላከያና የአማራ ልዩ ኃይል በመኖራቸውና የሠራዊቱን ጀግንነት ለታሪክ የሚያስቀምጡ ጋዜጠኞቸ በመኖራቸው እድለኛ ናት" ብለዋል።


የሕግ ማስከበር ዘመቻው የመሪ፣ ህዝብና ሠራዊቱ አንድነት የታየበት እንደነበር አስታውስው፤ ወደ ፊትም አገር የምትቀጥለው እንዲህ አይነት ቅንጅት ሲኖር መሆኑን ገልጸዋል።

የብዙ ሰዎች ገድል ታሪክ ሳይጻፍ መቆየቱን ጠቁመው፤ የአሁኑ ዘመቻው ሲጠቃለል የሚቀረው ታሪክ ነውና ታሪኩን የመዘገብና የመንገር ተራም ለጋዜጠኞች የተተወ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው በአጠቃላይ ከ70 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለዘገባ መሰማራታቸው ተወስቷል።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እየዘከረ የሚገኘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ከግንባር ዘገባ ለተመለሱ ባለሙያዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።

ጋዜጠኞቹ ከዚህ በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በኩል የዕውቅና ምስክር ወረቀት እንደተበረከተላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም