"የአገር ሕልውና በምንም መልኩ ሊታለፍ የማይገባ ቀይ መስመር ነው" - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
"የአገር ሕልውና በምንም መልኩ ሊታለፍ የማይገባ ቀይ መስመር ነው" - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ህደር 30/2013 (ኢዜአ) "የአገር ሕልውና በምንም መልኩ ሊታለፍ የማይገባ ትልቁ ቀይ መስመር ነው" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቷ ትናንት ምሽት በተካሄደው 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በመድረኩ የሕዝብና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች ታድመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሀዲው የህወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት በተባባረ ክንድ መቀልበሳቸውን ተናግረዋል።
የብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አጥፊዎቹን ለሕግ የማቅረቡ ስራ በስኬት እየተከናወነ ባለበት ጊዜ መከበሩ ሁነቱን ልዩ እንደሚያደርገውም ገልፀዋል።
'ብዝሃነታችን የምንደምቅባቸው ጌጦቻችን እንጂ የልዩነት አጥርና የግጭት መንስኤ ሊሆኑ አይገባም' ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ አደም የልዩ ፀጋዎች ባለቤት መሆናችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያመጡልን ዕድሎች አድርገን መጠቀም አለብን ብለዋል።
በመሆኑም ዜጎች በግል ማንነታቸው ኮርተውና በጋራ ማንነታቸው ደግሞ በህብር ደምቀው እንዲቆሙ ማስቻል ለነገ የማይባል የቤት ስራ መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል የተቃጣውን ሙከራ በጥበብ ለመከተው ሠራዊት ምስጋና አቅርበዋል።
መንግስት የሕግ ማስከበሩ ተግባር በስኬት እንዲከናወን በማድረጉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ አማካኝነት በርካታ አኩሪ ታሪኮችን የጻፈች አገር መሆኗንም ነው ያነሱት።
በሌላ መልኩ በገዛ ልጆቿ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድም የወንድሙን ሕይወት ቀጥፏል፤ ከቤት ንብረቱ አፈናቅሏል፤ ተሸማቆ አንዲኖርም አድርጓል ብለዋል።
ከውድቀቶቻችን መማር ባለመቻላችን ብዙ ዋጋ ከፍለናል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከመቆዘም ይልቅ አስከፊ ታሪኮቻችን እንዳይደገሙ ከችግሮቻችን መማር ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
መውደቅና መነሳት ተፈጥሯዊ ቢሆኑም የአገርን አቅም ክፉኛ እንደሚያዳክሙ በመጠቆም።
"ሁላችንም ኢትዮጵያ በምትባል መርከብ ላይ ተሳፍረናል" ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሕልውናዋን የሚፈታተን ሲመጣ 'አንታገስም' ነው ያሉት።
ለማንኛውም ነገር የማይታለፍ ቀይ መስመር አለ፣ ይህ ከታለፈ ግን አደጋው በሁላችንም ላይ በመሆኑ በዝምታ ሊታለፍ አይችልም ብለዋል።
"የአገር ሕልውና ደግሞ የማይታለፍ ትልቁ ቀይ መስመር ነው" ሲሉም አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመሆኑም "የዛሬ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነገ የአገር መሪ እንደሚሆኑ አስበው፤ የዛሬ ወጣቶች ደግሞ ነገ አገር እንደሚረከቡ ተገንዝበው በአገር ሕልውና ላይ ጠንካራ አቋም ሊይዙ ይገባል" ብለዋል።
በመድረኩ ክልሎች በተለይ ለሕዳሴ ግድብ እያደረጉት ላላው አበርክቶ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋ ነዋሪዎች ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለግድቡ ግንባታ 800 ሚሊዮን ብር ማዋጣታቸውን ገልጸዋል።
እስከ መጪው ጥር መጨረሻ ገቢውን ወደ አንድ ቢለዮን ብር ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውቀዋል።