ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሀዋሳ-ሞያሌ መንገድ እና የጋራ የፍተሻ ጣቢያ ን መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ ህደር 30/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አገራቱን የሚያስተሳስረውን የሞምባሳ-ናይሮቢ -አዲስ አበባ ኮሪደር ግንባታ አካል የሆነውን የሀዋሳ-ሞያሌ መንገድና የጋራ የፍተሻ ጣቢያ ፕሮጀክት መርቀው ከፈቱ።

መንገዱ ከሃዋሳ ከተማ እስከ ኬንያዋ አሲአላ ከተማ 1 ሺህ 3 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ እንዳለው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በኩል ያለው የመንገዱ ግንባታ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ገንዘቡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በድጋፍ የተገኘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመንገዱ ተመረቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የትራንስፖር አገልግሎትን የተሳለጠ እንደሚያደርገውም ገልፀዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው መንገዱ የቀጣናውን ንግድና ኢንቨስትመንት በማነቃቃት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሁለቱን አገራት ንግድና ኢንቨስትመንት አጠናክሮ ለማስቀጠል የኬንያ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ መሪዎች የቀጣናውን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በሃዋሳ-ሞያሌ መስመር የተበላሹና ያልተጠናቀቁ መንገዶችን በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም