በሕግ ማስከበር ዘመቻው ለዘገባ የተሰማሩ ጋዜጠኞች የሙያውን ስነ ምግባር ጠብቀው እንደሰሩ የብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ለዘገባ የተሰማሩ ጋዜጠኞች የሙያውን ስነ ምግባር ጠብቀው እንደሰሩ የብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 30/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በተከናወነው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለዘገባ የተሰማሩ ባለሙያዎች የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር አክብረው ሃላፊነታቸውን እንደተወጡ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ሚዲያ ተቋማት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በዘገባ ለተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዕውቅና እና የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ “በህግ ማስከበር ስራው ላይ የነበሩት ዘገባዎች የሙያውን ስነ ምግባር የተከተሉ ነበሩ” ብለዋል።
በስፍራው ተሰማርተው የዘገቡ ጋዜጠኞች ያሳዩት ሙያዊ ብቃት ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት በቀጣይም በምሳሌነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ሉአላዊነትን የማክበርና ህግን የማፅናት ስራውን እንዳገዙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ “ኢትዮጵያ የሠራዊቱን ጀግንነት ለታሪክ የሚያስቀምጡ ጋዜጠኞቸ በመኖራቸው እድለኛ ናት" ብሏል።
የሕግ ማስከበር ዘመቻው የመሪ፣ ህዝብና ሠራዊቱ አንድነት የታየበት እንደነበር አስታውስው፤ ወደ ፊትም አገር የምትቀጥለው እንዲህ አይነት ቅንጅት ሲኖር መሆኑን ገልጿል።
ዘመቻው ሲጠቃለል የሚቀረው ታሪክ ነውና ታሪኩን የመዘገብና የመንገር ተራ ለጋዜጠኞች የተተወ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁሟል።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው በአጠቃላይ ከ70 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለዘገባ መሰማራታቸው ተወስቷል።
80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እየዘከረ የሚገኘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ከግንባር ዘገባ ለተመለሱ ባለሙያዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ጋዜጠኞቹ ከዚህ በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በኩል የዕውቅና ምስክር ወረቀት እንደተበረከተላቸው ይታወሳል።