ቀጥታ፡

የህወሃት መውደቅ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያነሳሳ መሆኑ ተገለጸ

ደሴ ህዳር 30 ቀን 2013 (ኢዜአ ) የህወሃት መወገድ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ሆነው ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ገለጹ።

"የህዝባችን እኩልነትና አንድነት ለጋራ ብልጽግና"  መሪ ሀሳብ 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በደሴ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የከተማዋ  አስተዳደር ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ አህመድ ሙህዬ በወቅቱ እንዳሉት ህወሃት በሀገሪቱ ህዝቦች ላይ ለዘመናት የዘለቀውን መፈቃቀርና መተሳሰብ በመናድ ያለመተማመን እኩይ ሴራ ፈጽሟል።

በዚህም በተከተለው ኢፍትሃ የፖለቲካ አካሄድ  አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ ህዝቡን ለእርስ በእርስ ጥርጣሬ ዳርጎት ነበር ብለዋል።

በየዓመቱ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በዓለም የራሱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍላጎት በሚያሳካ መልኩ የሚካሄድ እንጂ ለእውነተኛ መፈቃቀርና መተሳሰብን በሚገነባበት መንገድ እንዳልነበር አውስተዋል።

አሁን ላይ የጥፋት ሃይሉ በመከላከያ ላይ የፈጸመው  ጥቃትና የሀገር ክህደት ተከትሎ በተባበረ ክንድ እንዲወገድ መደረጉን ጠቁመው ይህም ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ ሆነው ትክክለኛ ፌደራሊዝም እንዲተገብሩ በር የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።

የቡድኑ  መወገድ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እንደሚያነሳሳ  አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ጀማል ሰይድ "የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከለውጡ በፊትና በኋላ" ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ህወሓት በተከተለው የሴራ ፖለቲካ ህዝብን ሲጨቁን፤ ሲገርፍና ሲያሳደድ መኖሩን አውስተዋል።

ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ በመምስል ህዝብ ሲያታልልበት የነበረው  አካሄድ ራሱን ጭምር እንደጎዳው ጠቁመዋል።

የለውጡ አመራር ከመጣ ወዲህ በርካታ አፋኝኛ ጨቋኝ ህጎች ከመሻሻላቸውም ባለፈ ህዝቡ በነጻነት እንዲናገር፣ እንዲጽፍና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የሚጠቀምበት ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ለውጡን በማስቀጠል  እውነተኛ ዲሞክራሲ ሰፍኖ እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ህዝቡ የበኩላቸውን  ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ  ወይዘሮ ፈንታዬ አብርሃ በሰጡት አስተያየት በዘመነ ወያኔ የይስሙላ ዴሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋት ልዩነትን መሰረት ያደረገ ትርክት በመፍጠር ሀገር የማፍረስ ተግባር ላይ ተጠምዶ መቆየቱን አስታወሰዋል።

ለዚህም በሐሰት ፕሮፓጋንዳ  በማታለል ህዝብን እያሳቀየ የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ  ከበደል ላይ በደል ሲፈጽሙ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

"እስካሁን ሲከበር የነበረው በዓልም የይስሙላ ነበር ያሉት" ወይዘሮ ፈንታዬ አሁን ላይ ወያኔ በመውደቁ ከዚህ በኋላ ትክክለኛ ዲሞክራሲ በማስፈን  ዜጋው በሁሉም ዘርፍ  እኩል  ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት እንደለበት ተናግረዋል፡፡

"አንድነታችን አጠናክረን እንደየ እምነታችንና ባህላችን ተሳስበን የምንኖርባትን ኢትዮጵያ መመስረት የሁላችን ኃላፊነት ነው" ያለው ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ናሁሰናይ አሰፋ ነው፡፡

ፓርቲዎችም ከድብብቆሽ ፖለቲካ ተላቀው እውነተኛ ዲሞክራሲ በመመስረት ታሪካቸውን ማደስ ይጠበቅባቸዋል ሲልም ገልጿል፡፡

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት አመራሮች፣የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም