ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ሕግ ማስከበር እርምጃው በማስረዳት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ህዳር 30/2013 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሕግ ማስከበር እርምጃውን በትክክል እንዲገነዘብ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ዳያስፖራው ለሠብዓዊ ድጋፍ 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማበርከቱንም ገልጿል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በህወሓት ቡድን ላይ የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ተጠናቆ ተልዕኮው ወደ 'ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ' መሸጋገሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ሠራዊቱ ላይ በተፈፀመው ጥቃት የዳያስፖራው ስሜት የነበረው የመደናገጥ፣ የመጨነቅና ስለ ጉዳዩ ማብሪሪያ የመጠየቅ እንደነበር ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ሚሲዮኖችን፣ በውጭ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሌሎች የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተፈፀመውን ጥቃትና የሕግ ማስከበር እርምጃውን አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ የማድረስ ስራ መከወኑን ተናግረዋል።

መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ የገባበትን ምክንያት በግልጽ በማስረዳት "የህወሓት ቡድን" የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲሰራ የነበረውን ተግባር እንዲገነዘቡት ተደርጓል ብለዋል።

በተለይም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የነካ በመሆኑ መንግስት ሕግ ከማስከበር በቀር አማራጭ እንደሌለውና እርምጃው ባይወሰድ በአገር ላይ ይደርስ የነበረውን አደጋ በማስረዳት የእርምጃውን አውድ እንዲያውቁት መደረጉን አብራርተዋል።

ለዳያስፖራው ጉዳዩን እንዲገነዘቡት ብቻ ሳይሆን በሚኖሩበትና በሚሰራባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለዲፕሎማቶች ማብራሪ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ዳያስፖራውም ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሕግ ማስከበር እርምጃውን በትክክል እንዲገነዘብ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

ጥቂት ዳያስፖራዎች የሕግ ማስከበር እርምጃውን በተዛባ መልኩ በመተርጎም የእርስ በእርስ ጦርነት ነው በማለት ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው በማስመስል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር ሲሰሩ እንደነበረም ጠቁመዋል።

ይሁንና አብዛኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በውስን ዳያስፖራዎች የሚቀርቡ የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ ትክክለኛውን መረጃ የማሳወቅ ስራ መስራቱን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ዳያስፖራው ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተቸገሩ ወገኖች ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ያሳየው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስረዱት።

በአገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ውስጥ ኤጀንሲው የሚመራውና የዳያስፖራውን ድጋፍ የሚያስተባብር ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በሶስት ሳምንት ጊዜ ዳያስፖራው በገንዘብና በአይነት 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አገር ወዳድነቱን ማሳየቱንም ተናግረዋል።

ድጋፉ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእስያ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች መሰባሰቡን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ለጥቂት ትርፍ ብለው ገንዘባቸውን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚልኩ ዳያስፖራዎች እንዳሉ ጠቁመው ይህ የአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ ያተኮረና ለአገር የማይጠቅም መሆኑን አስታውቀዋል።

ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያን የሚወዱ ከሆነ ሕጋዊ የገንዘብ መላኪያ አማራጮችን ተጠቅመው መላክ እንደሚገባቸው ነው ወይዘሮ ሰላማዊት ያሳሰቡት።

ከለውጡ በኋላ መንግስት የዜጎችን ክብር መሰረት ባደረገው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዜጎች የአገራቸው አምባሳደር በመሆን ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ መስራቱን ገልጸዋል።

በዚህም ቀድሞ የነበረው በሚሲዮኖችና ዳያስፖራዎች የንትርክ፣ ያለመተማንና ያለመግባባት ተቀይሮ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል ብለዋል።

ዳያስፖራው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠርና በ"ገበታ ለአገር" ፕሮጀክት ድጋፍ በማድረግ ለአገሩ አለኝታነቱን እያሳየ መሆኑንም አንስተዋል።

በሚሲዮኖችና በዳያስፖራው መካከል የተፈጠረው ትብብር የሕግ ማስከበር እርምጃው ሲወሰድ ጉዳዩን ለማስረዳትና በቅንጅት ለመስራት ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩንም አክለዋል።

ዳያስፖራው ልዩነቶች ቢኖሩትም በአገሩ ጉዳይ ያሳየውን አንድነትና ትብብር በማሳደግ አገሪቷን በሚጠቅሙ የልማትና የዕድገት ስራዎች ላይ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም