መገናኛ ብዙሃን የሴቶች ጥቃትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የሴቶች ጥቃትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ማጠናከር አለባቸው
አዲስ አበባ ህደር 30/2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን በሴቶች ጥቃትና በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል ላይ የሚያደርሷቸውን መረጃዎችና የግንዛቤ ማሳደጊያዎች ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እነዚህን ጉዳዮች አጀንዳ በማድረግ ተከታታይ ሥራዎችን እንደሚሰራም ተገልጿል።
ኢዜአ ዓለምአቀፉን የፀረ-ፆታዊ ጥቃትና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የግንዛቤና ንቅናቄ ባለሙያ አቶ ደስታው ገበያው አካሄዱን እየቀረ የመጣውን የሴቶች ጥቃት ለመቀነስ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የንቅናቄና የግንዛቤ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከኃይማኖት አባቶች ጋር የንቅናቄና ግንዛቤ ሥራዎቹ እየተሰሩ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ይሁንና መገናኛ ብዙኃን ከሚኒስቴሩ ጋር በመሆን በሴቶች ጥቃትና በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የንቅናቄ ሥራዎችን በስፋት መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ከግንዛቤ መፍጠር ባሻገር አጥፊዎችን በመቅጣት ረገድ የሚታዩ የሕግ ክፍተቶችና ተፈፃሚነት ችግሮችን ለማረም ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚዲያው "ከእኛ ጋር ሆኖ የንቅናቄ ስራውን በሰፊው መስራት አለበት" ያሉት አቶ ገበያው ለአብነት የተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን ተሞክሮ፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ታሪክና ጥሩ የሰሩ አገራት ተሞክሮዎች ጠቁመዋል።
በእነዚህ ጉዳዮች መነሻነት መረጃዎችን፣ ዶክመንተሪና ሌሎች ዘገባዎችን ሚዲያው በስፋት መስራት አለበት ብለዋል።
የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ የኤች.አይ.ቪ አገራዊ ሥርጭት ምጣኔ ዜሮ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ቢሆንም አሁንም መቀነስ ባለበት ልክ እየቀነሰ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በማኅበረሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ ለተያዘው ራዕይ መሳካትና ለቫይረሱ መቀነስ መገናኛ ብዙኃን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ሚዲያው ችግሩንም፣ ቁጥሩንም ያውቃሉ በመሆኑም የኤች.አይ.ቪን ጉዳይ ስራዬ ብሎ ሊይዘው ይገባል" ብለዋል።
በሽታውን በመከላከል ረገድ አመርቂ ውጤቶች አስመዝግበን ነበር ያሉት አቶ ክፍሌ አሁን ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።
"መዘናጋቱ ለምን ተፈጠረ፣ ማን ምን መስራት አለበት የሚለውን ለሚዲያው የምናሳስበው ትልቁ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
የኢዜአ ባለሙያዎች የንጉስነሽ ውቤና ሂርጳ ሰርቤሳ በበኩላቸው የሴቶች ጥቃትና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጉዳይ የማኅበረሰብ ችግር በመሆኑ አጀንዳ ሆኖ በተከታታይ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ሴቶችን የሚመለከት ጉዳይ የዘወትር ስራችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
"የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ በአንድ መድረክ ወይም አንድ ጊዜ ተነስቶ የሚያበቃ" አይደለም የሚለው ሂርጳ ተከታታይነት ያለው ስራ ከመስራት ባሻገር የስራችን ዋነኛ አካል መሆን አለበት" ብሏል።
ምክንያቱም "ሴቶች የአገር ምሰሶ ናቸው" ሲል አክሏል።
በኢዜአ የሴቶችና ዘርፈብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ቦጋለና የስራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በልስቲ አለምነህ በተቋሙ ስርዓተ ፆታ ላይ ያተኮሩ ዘገባዎች እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
ይሁንና ከተቋሙ ዕድሜ ጠገብነት፣ ካለው የሰው ኃይልና ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ ብዛት አንፃር ተከታታይና ሰፊ ስራዎችን መስራት እንዳለበት ነው የገለጹት።
እንደ ወይዘሮ ታደለች ገለፃ ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት እነዚህ ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ ባይጠፉ እንኳን የሚቀንሱበትን መንገድ ለመፍጠር ሚዲያው ከፍ ያለ ሚና አለው።
በኤች.አይ.ቪም ሆነ በፆታዊ ጥቃት በአብዛኛው ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን ያነሱት አቶ በልስቲም "ሴቶች ላይ መስራት ማለት ወጣት ላይ መስራት፣ አገር ማትረፍ እና አገር ማቆየት ነው" ሲሉ ነው የገለጹት።
በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በእነዚህ ጉዳዮች በሰፊው "መስራት አለብን" ብለዋል።
የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተፈራ በቀለ የፆታዊ ጥቃትና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ተከታታይነትያለው ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢዜአ በቀጣይም አጃንዳዎቹን የሚዲያዎች አጀንዳ አድርጎ በተከታታይ የሚሰራባቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
በኤዜአ በተካሄደው የፓናል ውይይት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የፀረ-ሙስና ቀንን ታሳቢ ያደረጉ ሰነዶች ቀርበዋል።