ቀጥታ፡

በጎ አድራጎት ድርጅቶች በጸረ-ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጸረ-ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ የተባበሩት መንግሥታት ሥነ-ህዝብ ፈንድ ጠየቀ።

ድርጅቱ የ16ቱ ቀናት የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄን አስመልክቶ የፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ ግብሮች ዛሬ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የፈንዱ ምክትል ተወካይ ሳራህ ማሳላ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለ እድሜ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ወንጀል ቢሆኑም፤ ከእምነትና ባህል ጋር ባላቸው ትስስር አሁንም በመተግበር ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ባህልና እምነት በማህበረሰቡ ባላቸው ተቀባይነት እምነትን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለማህበረሰቡ ካላቸው ቅርበትና ተቀባይነት አንጻር ጾታዊ ጥቃትን እንዲከላከሉ ጠይቀዋል።

ፈንዱ ኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ ጾታዊ ጥቃቶች ከባህል፣ እምነትና ሞራል ያፈነገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሐጂ ሱልጣን አህመድ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በመሥራት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።                            

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይልቃል ሽፈራው ኮሚሽኑ ጾረ-ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ግን ቀጣይነትና የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ተወካይ ማህሌት አማረ ኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሕግ፣ ፖሊሲና የተቋማዊ  ግንባታ ተግባራትን ብታከናውንም፤ጥቃቶች እንዳልቀነሱ ገልጸዋል።

ጥቃቶችን ለመቀነስም ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የተመሰረቱ ተቋማትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጸረ ጾታዊ ንቅናቄ ከህዳር 16 እስከ ታህሳስ 1 ቀን የሚቆይ ሲሆን፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ በመፍጠር በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከበር ነው።

በዓለም ላይ ከሶስት ሴቶች አንዷ አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባት የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2016 የተደረገው የሥነ-ህዝብና ጤና የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች መካከል 23 በመቶ አካላዊ፣ 10 በመቶ ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ይደርስባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም