ቀጥታ፡

ብዝሃነታችን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የምናጎላበት እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም - አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29/2013 (ኢዜአ) “ብዝሃነታችን የምንዋብባቸው፣ የምንደምቅባቸውና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጉልተን ለዓለም አደባባይ የምናሳይባቸው እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም” ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።

15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማጠቃለያ ዝግጅት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።

ቀኑ የሚከበረው ህዳር 29 ቀን የጸደቀውን ህገ መንግስት ለመዘከር፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲተዋወቁ፣ ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩና በህገ መንግስቱ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ታስቦ የሚከበር ነው።

የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት ቆይታቸው ዘመን የጋራ እሴቶችን ያዳበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመተማመንና በመተባበር አገር ያቆሙ አገራቸውን ከጠላት ለመከላከል በጋራ የተሰለፉ፣ የተዋደቁና የተሰዉ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኔ የሚሉት ማንነት ያላቸው ናቸው” ብለዋል።

“ብዝሃነታችን እንደልብስ የምንዋብባቸው፣ እንደጌጥ የምንደምቅባቸውና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጉልተን ለዓለም አደባባይ የምናሳይባቸው እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ሰላምን በማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ፈጣንና ሁለንተናዊነት ያለውን ልማት በማረጋገጥ ረገድ ብዝሃነቱ የበለጠ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

ብዙሃነቱ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት የሚቀጠፍበትና ሃብት የሚወድምበት ሊሆን እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ህዝቦች የግላችን በሚሉት ማንነታቸው ሊኮሩ እና የጋራ በሆነው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው በህብር እንዲቆሙ በመከባበር፣ በወንድማማችነትና በመተማመን ላይ የተመሰረ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ለነገ የማይባል የቤት ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ባለፉት ሁለት የለውጥ አመታት በተቃርኖ የቆሙ ሁለት ገቢሮችን አገሪቱ ስታስተናግድ መቆየቷን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ የሚታትሩ ሃይሎችና የግልና የቡድን ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች እንደታዩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም