የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በህግ ማስከበር ዘመቻ ዘገባ ለተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በህግ ማስከበር ዘመቻ ዘገባ ለተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጠ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በህግ ማስከበር ዘመቻ በዘገባ ላይ ለተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጠ።
ድርጅቱ 80ኛ የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም ሚዲያ ተቋማት በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በዘገባ ለተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጥቷል።
በእውቅና መርሃ ግበሩ ላይ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት ባለሙያዎች መረጃ በማድረስና ከወታደሩ እኩል ፈተናውን በመጋፈጥ የተሳፉበት ስራ ዕውቅናና ምስጋና መስጠት ያስፈልጋል።
በፅንፈኛው ከሃዲ ቡድን ጥቃት የተሰነዘረበት ኢትዮጵያዊነትና የአገር ሉዓላዊነት እንደሆነ ገልፀው፤ የችግሩን መጠን ከማሳየት በተጨማሪ በቀጣይ ኢትዮጵያዊነትና አገራዊ አንድነት ዳግም በአዲስ ተስፋ እንዲያንሰራራ ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነትና የቤት ስራ እንደተጣለባቸው ገልፀዋል ።
ባለሙያዎቹ ለነበራቸው ሚና የዕውቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬት በአምባሳደር ሬድዋንና በድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተበርክተዋል።
ጋዜጠኞች በግንባር ለዘገባ በተሰማሩበት ወቅት ባጋጠማቸውና በተመለከቱት ትዝብት አጋርተዋል።
ጋዜጠኞቹ ከዚህ በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በኩል የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።