ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚንቀሳቀስባትና የዜጎች ክብር የሰፈነባት እንድትሆን መትጋት ያስፈልጋል-ም/ጠ/ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2013(ኢዜአ)  ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚንቀሳቀስባትና የዜጎች ክብር የሰፈነባት፤ ሁሉም የየራሱን ማንንት በነጻነት የሚያንጸባርቅባት እንድትሆን መትጋት እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በአገር አቀፍ ደረጃ 15ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት አገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ሕዝቦችን ያራራቁ ግንቦች እየፈረሱ ናቸው።

የለውጥ ጉዞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአብሮነትና በአንድነት ወደ ብልጽግና የሚያሻግራትን ጎዳና ለመዘርጋት እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ በትልቁ ለሕዝቦቿ የምታስፈልገው ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚንቀሳቀስባት፣ የዜጎች ክብር የሰፈነባት የተሻለች አገር እንድትሆን መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ብሔር ብሄረሰብ የየራሱ ቋንቋ፣ ባህልና ትውፊትና ታሪክ በነጻነት የሚስተናገዱባት ስልጡን ምድር እንድትሆን ጠንክሮ መስራት ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።

ሁሉም በወንድማማችነት፣ በመተሳሰብና አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን ለሕብረ ብሔራዊ አንድነቱ ዘብ እንዲቆምም ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ በአገሪቷ በብዙ ዘርፎች እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት ከፍተኛ የዴሞክራሲ እጦት፣ ሥራ አጥነትና የሰብአዊ መብት በሰፊው ይስተዋል እንደነበር አንስተዋል።

ይህ ሁሉ ችግር ተደምሮ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ለውጥ እንዲመጣ መታገላቸውንና የለውጡ አመራርም የተሻሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ እስካሁን ባለው ሂደት ከብሔር ብሔረሰቦች መብት አንጻር ምን ጥቅሞች እንደተገኙና የሚቀሩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። 

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሓመድም፤ ከለውጡ በኋላ የተሻሉ ሁኔታዎች መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ቢቀር በዚህ ወቅት ሕዝቦችን የሚያቀራረቡ ትርክቶች መጀመራቸውንና ከፋፋይ አስተሳሰቦች እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሚዛናዊ የፖለቲካ ውክልና እየመጣ መሆኑና ከዚህ በፊት አጋር ተብለው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚታዩ ክልሎች ከሌሎች ጋር እኩል በመሆን አንድ ላይ ተቀምጠዋል ነው ያሉት።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስም በተለያዩ ሁኔታዎች አመቺ ያልሆኑ ሕጎች መሻሻላቸውን አንስተዋል።

ከተሻሻሉት ሕጎች መካከል ጥቅል የሆነውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ለአተገባበር በሚያመች መልኩ መሻሻሉን ጠቅሰዋል።

በአንጻሩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በመተግበር ኢትዮጵያ ምን እንደተጠቀመችና ያገኘችውን ጥቅምና ጉዳት መተንተን አለበት የሚሉም ተሳታፊዎች ነበሩ።

ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ዋቢ አድርገው  የሕገ መንግሥት መሻሻል ያለውን ጥቅም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለም በሕገ መንግሥቱ ላይ ክፍት ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም