በዓሉን የምናከብረው ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በገባንበት ወቅት ነው... ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉን የምናከብረው ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በገባንበት ወቅት ነው... ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ
አዳማ፤ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ) የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የምናከብረው ወደ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በገባንበት ወቅት ነው ሲሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገለጹ።
በዓሉ የሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑ እና 46 የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ በውይይት ተከብሯል።
ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት የ15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የተከበረው በሀገሪቱ ከማስመሰል ፌዴራልዝም በመውጣት ወደ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በተገባበት ወቅት ነው።
"ባይተዋርነት ቀርቶ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ወደ ውሳኔ ሰጪነት የመጡበት ወቅት ላይ ነን፤ አካታች የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት ለመገንባት የያዝነውን ግብ ከዳር ለማድረስ ዳግም ቃላችንን የምናድስበት መሆን አለበት" ብለዋል።
በበዓሉ ከታደሙት መካከል የቀብሪዳሃር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አብድልፈታህ አህመድ እንዳሉት የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የተከበረው ጁንታው ህወሃት ተወግዶ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ድል በተመዘገበበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋለ።
ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸውን ሰላም በመጠበቅ አንድነታቸውን አጠናከረው ለውጡን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቁርጠኝነታቸውን ዳግም የሚያረጋግጡበት ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የይስሙላ ክልል ተሰይሞላቸው አጋር ተብለው የነበሩ ብሔረሰቦች
ወደ ውሳኔ ሰጪነት የመጡበት ነው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዑባ ሙሐመድ ናቸው።
የተገኘውን መልካም እድል በመጠቀም ለውጡን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመጠበቅ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሁን ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትና የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የሚያስችላቸውን መልካም አጋጣሚ ያገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል።
"ህብረብሔራዊነት መገለጫችን ነው፤አንድነት ህልውናችን ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው በዓል ላይ የየዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶችና ምክትሎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ተገኝተዋል።