ቀጥታ፡

የመዲናዋ ግንባታና ዲዛይን ኤጀንሲ ከ26 ሺህ በላይ ቤቶች የዲዛይን ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ) የመዲናዋ የግንባታና ዲዛይን ኤጀንሲ በ2013 በጀት አመት አስተዳደሩ ለሚያስገነባቸው ከ26 ሺህ በላይ ቤቶች የተሟላ ዲዛይንና የስራ ዝርዝር ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቋል፡፡

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የያዛቸውን ተግባራት አስመልክቶ ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ አያሌው እንደገለጹት "ኤጀንሲው በበጀት አመቱ በመዲናዋ ለሚገነቡት 26 ሺህ 80 ቤቶች የተሟላ ዲዛይን እና የስራ ዝርዝር ለማዘጋጀትና ድጋፍና ክትትሉን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡"

ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲው 2 ሺ 200 የኪራይ ቤቶች ላይ የዲዛይን ስራ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው በዚህ አመት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ወደ ስራ በመግባቱ ነባር ፕሮጀክቶች ላይ ያሉ ግድፈቶችን ነቅሶ ለማየት መቻሉን ነው የተናገሩት።

በዚህም የዲዛይን አለመሟላት እና የውል አስተዳደር ዋነኛ ችግር እንደነበርም መለየት ተችሏል ብለዋል።

የተጠናቀቁ በርካታ ግንባታዎች የመሰረተ ልማት ስላልተሟላላቸው ለነዋሪው ማስረከብ እንዳልተቻለም ዳይሬከተሩ ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት የዝግጅት ምእራፍ እንደመሆኑ ተቋሙ ሰራተኞችን የማደራጀት፣ ግብአቶችን የማሟላት እንዲሁም የአቅም መገንቢያ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱንም ነው የተናገሩት።

በዚህም ተቋሙ እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል አቅም መገንባቱንም አብራርተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የተቋሙ ሰራተኞችም የኤጀንሲውን እቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው አገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ በ2013 ዓ.ም በአዲስ መልክ ወደ ስራ የገባ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ በግንባታ ወቅት የሚታዩ የዲዛይን ግድፈቶችና እና ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የሚታየውን የስራ መጓተት ለመፍታት ታስቦ መቋቋሙ እንዲሁ።

በውይይቱ ማጠናቀቂያ የኤጀንሲው ሰራተኞች በአንድ አመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የወር ደመወዛቸውን 50 በመቶ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም