ከለውጡ በኋላ የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል --- ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ - ኢዜአ አማርኛ
ከለውጡ በኋላ የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል --- ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ) የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ባደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻሻለ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን "ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንትጋ" በሚል መሪ ሃሳብ በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የፌደራሉ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተስፋዬ ዳባ በእዚህ ወቅት እንዳሉት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአሰራር ለውጥ ካደረጉ ተቋማት መካከል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ለ27 ዓመታት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸው ከነበሩ ተቋማት መካከልም አንዱ ማረሚያ ቤቶች እንደነበር አስታውሰው፣ ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ባደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች በታራሚዎች አያያዝ ላይ ይስተዋል የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል ብለዋል።
"ኮሚሽኑ አሁን እያሳየ ያለውን በጎ ተግባር በማስቀጠል በኢትዮጵያ ለተጀመረው የዴሞክራሲና የብልጽግና ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በታራሚነት ካሳለፉ ግለሰቦች መካከል የ"ሴንተር ፎር ጀስት ግብረሰናይ ድርጅት" ዳይሬክተር አቶ ኩምሳ ጉደታ በበኩላቸው የማረሚያ ተቋማት የለውጥ ሥራ በተጨባጭ ታይቷል ብለዋል፡፡
በድርጅታቸው በኩል ወደ ማረሚያ ቤቱ ለስልጠና ዳግም በመጡባቸው ጊዜያት ቀደም ሲል በማረሚያ ቤቱ ይፈጸሙ የነበሩ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአሁኑ ወቅት ተሻሽለው ማየታቸውን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ የለውጥ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ወንድሙ ኮሚሽኑ በዘረጋው የለውጥ ሥራ አመራር የህግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥሱ አሰራሮችና ተግባራት ተወግደዋል ብለዋል።
ቀደም ሲል የህግ ታራሚዎችን በጨለማ ቤቶች ማቆየት፣ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በታራሚዎች ላይ የሚፈጸሙ የድብደባና መሰል የኃይል እርምጃዎች አለመኖራቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ምስጋናው ኤርሚያስ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ሥራዎች ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል።
"ማረሚያ ቤቶች ስማቸው መነሳት ያለበት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳይሆን ታራሚን በአግባቡ አርሞና አምራች ኃይል አድርጎ ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል ነው" ያሉት ደግሞ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል አባሶ ናቸው።
ለዚህም የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅት አራት የኢንዱስትሪ ማዕከላትን በመገንባት ታራሚውን አምራች ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን በከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ሲከበር የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የታራሚዎች የሥራ ውጤቶችም ተጎብኝተዋል፡፡
1313