ቀጥታ፡

በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ላይ ዐቃቤ ህግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንዲደመጡለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ) በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ላይ ዐቃቤ ህግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ይደመጡልኝ በማለት ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ።

ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ላይ የማቀርባቸው ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ ይሰሙልኝ ሲል ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ይሕንን ተከትሎም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ- መንግስት እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በክስ መዝገቡ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ የማሰማቸው ምስክሮቼ ለደህንነታቸው ሲባል በምስክር ጥበቃ አዋጅ መሰረት ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ይመስክሩልኝ ሲል አመልክቶ ነበር።

በዚህ የክስ መዝገብ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወይዘሮ ቀለብ ሥዩም፣ ወይዘሮ አስካለ ደምሌና በዋስትና ከእስር የተፈቱት አቶ ጌትነት በቀለ ይገኙበታል።

ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን ይደመጥ ማለቱ ተገቢነት የለውም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።

የተከሳሽ ጠበቆችም እንዲሁ ተከሳሾች በእነሱ ላይ የሚመሰክረው ማን እንደሆነ የማወቅ ሕገ-መንግስታዊ መብት አላቸው ሲሉም ተደምጠዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የምስክር አቀራረብ ሒደት ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ጥያቄ የተከሳሾችን ሕገ-መንግስታዊ መብት የሚነካ በመሆኑ ተቀባይነት እንዳላገኘም አስታውቋል።

በዚሁ የክስ መዝገብ ስድስተኛና ሰባተኛ ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ ማቅረብ ባለመቻሉና አድራሻቸውም የማይታወቅ በመሆኑ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ክሱ እንዲቋረጥ የተደረገው ፖሊስ ተከሳሾቹን በተሰጠው ጊዜ ፈልጎ ማቅረብ ባለመቻሉ በማረሚያ ቤት ላሉ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ተብሏል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ ላይ የተሻሻለ ክስ ለመጠባበቅ ለታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም