በደሃው የትግራይ ህዝብ ልጅ ላይ የሚቆምሩ አንዳንድ ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደሃው የትግራይ ህዝብ ልጅ ላይ የሚቆምሩ አንዳንድ ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2013 ( ኢዜአ) በውጭ አገራት ተደላድለው እየኖሩ በደሃው የትግራይ ህዝብ ልጅ ላይ የሚቆምሩ አንዳንድ ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።
በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በመደገፍ ለህዝቡ የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራት የትግራይ ህዝብን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ የማነ ንጉስ "በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን ለውጥ በውጭ አገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ሊደግፉ ይገባል" ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትግራይን መልሶ ለማቋቋም እና ወደ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረትም እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
የትግራይን ህዝብ ጥቅም እና ህልውና ማረጋገጥ የሚቻለው በመተባበር እና በመደጋገፍ ስለሆነ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ በተቃራኒ በውጭ አገራት ተደላድለው እየኖሩ በደሃው የትግራይ ህዝብ ልጅ ላይ የሚቆምሩ አንዳንድ ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል አቶ የማነ።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጊደና መድህን፤ "በተለይም በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ክልሉን ወደ ሰላምና ልማት ለመመለስ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው" ብለዋል።
በህግ ማስከበሩ ወቅት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉትን ለማቋቋምና በጁንታው የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትም የዳያስፖራው ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍም የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።
ተጋሩ የኢትዮጵያዊያን ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዩሐንስ ጎይቶም በበኩላቸው በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች የህወሓትን እኩይ ፅንፍ መቀበል የለባቸውም ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን የሚሻ በመሆኑ ለዚህ ስኬት መደገፍ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠርና የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባም ነው አቶ ዮሐንስ ያመለከቱት።