ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ 12 የኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው

ጎባ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የብርሃን ለሁሉም ፕሮጄክት በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ 12 ኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የብርሃን ለሁሉም ፕሮጀክት  በምሥራቅ ባሌ ዞን የለገ ሂዳ ወረዳ ጣቢያ ሱፐርቫይዘር አቶ ኤሊያስ ይሻው ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው በብርሃን ለሁሉም ፕሮጀክት "ቤልቱ" ከተማና በህማ ቀበሌ ላይ በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ ማዕከላት እየተገነቡ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በወረዳው እያስገነባቸው የሚገኙና በቅርቡ ተጠናቀው  ለአገልግሎት እንደሚበቁ የሚጠበቁት ሁለቱ ማዕከላት  በ2 ሚሊዮን 300ሺህ  የአሜሪካን ዶላር በጀት የሚካሄዱ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በወረዳው እየተገነቡ የሚገኙት ሁለቱ ማዕከላት አገልግሎት ሲጀምሩ 950 ኪሎ ዋት የማመንጨት አቅም እንደሚኖራቸው አመልክተዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የብርሃን ለሁሉም ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ሁሉንአየሁ ደጀኔ እንደተናገሩት ፤ኢትዮጵያ ለጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ 12 የኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡

በብርሃን ለሁሉም ፕሮጀክት በለገ ሂዳ ወረዳ እየተገነቡ የሚገኙ ማዕከላትም የዚሁ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙት በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ የብርሃን ማስጫ ማዕከላት እየተገነቡ የሚገኙት በተለይም ከሀገሪቱ የኃይል ቋት በርቀት ላይ በሚገኙ  የአርብቶ አደር ማህበረሰብ አካባቢዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ይህም ያለባቸውን የኃይል አቅርቦት የማዳረስ ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙት የኤልክትሪክ ኃይል ማዕከላት ግንባታቸው ሲጠናቀቁ 3ሺህ 800 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡

የለገ ሂዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልናሲር አህመድ በበኩላቸው ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ በፀሐይ  የሚሰሩ የሃይል አቅርቦት ማዕከላት በአካባቢው  መገንባታቸው  አገልግሎቱን ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  ለማዳረስ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል፡፡

አስተዳዳሪው እንዳሉት ወረዳው ለፕሮጀክቱ ስኬት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ በንቃት እየተሰተፈ ነው፤  ፕሮጀክቱ ለሚፈለገው ዓላማ እስኪበቃ ድረስ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ሼህ አልይ ሁሴን የወረዳው ማዕከል የሆነችው  የቤልቱ ከተማ ረዥም እድሜ ያስቆጠረች ቢትሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷ የአካባቢው ማህበረሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት የዘመናት ጥያቄያችንን ሰምቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንድንሆን እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚያስመሰግነው ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ 

ፕሮጀክቱ በአካባቢያቸው  የስራ አጥነት ችግር በተወሰነ መልኩ ለማቃለል እንደሚያግዝ  የገለጸው ደግሞ  ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወጣት ላዚም አሎ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት  ከ4 ሺህ 400 በላይ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ላይ መድረሷን በኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም