ለሀገራችን እድገትና የጋራ ህልውናችን ስንል ተጋግዘንና ተደጋግፈን ልንጓዝ ይገባል ... የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራችን እድገትና የጋራ ህልውናችን ስንል ተጋግዘንና ተደጋግፈን ልንጓዝ ይገባል ... የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2013 (ኢዜአ) ለአገራችን እድገትና የጋራ ህልውናችን ስንል ኢትዮጵያዊያን ተጋግዘንና ተደጋግፈን ወደ ፊት ልንጓዝ ይገባል ሲሉ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ላይ የታደሙ ዜጎች ተናገሩ።
ለ15ተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በማስመልከት ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን በአዲስ አበባ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እንዳሉት ለአገራችን እድገትና የጋራ ህልውናችን ስንል ኢትዮጵያዊያን ተጋግዘንና ተደጋግፈን ወደ ፊት ልንጓዝ ይገባል።
ከሲዳማ ክልል የተገኙት አቶ አለሙ አዳሙ በአንድነት ፓርክ በነበራቸው ጉብኝት በተመለከቱት ሁሉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሁላችንንም የጋራ እሴቶች ይዞ ለህዝብ እይታ ክፍት በመሆነው ቤተ መንግስት በመገኘት ከመጎብኘታችን በተጨማሪ የጋራ ሃብታችን መሆኑንም ተገንዝበናል ብለዋል።
በአንድነት ፓርክ ኢትዮጵያን በትንሹ ያዩበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን አባላትን ወደ ህግ ለማቅረብ በነበረው የህግ ማስከበር ሂደት ኢትዮጵያዊያን ያሳዩትን ትብብር በአገራዊ አንድነትና የጋራ ልማትም ሊደግሙት ይገባል ነው ያሉት።
ከደቡብ ኦሞ ዞን የመጡት አቶ ደለለኝ ሰኔ፣ ከዚህ ቀደም የህወሓት ቡደን ስልጣኑን ለማቆየት ሲል አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር በጥርጣሬ እንዲተያይና ግጭት ውስጥ እንዲገባ አበክሮ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የሴረኛ ቡድኑ የጥፋት አካሄድ በህዝብ ተሸንፎ በመጨረሻም ለውድቀት መዳረጉን ገልጸው፣ ህዝቡ በቀጣይ ለአገራዊ አንድነቱ በጋራ ሊቆም ይገባዋል ብለዋል።
በአንድነት ፓርክ በተመለከቱት ነገር ሁሉ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ከሐረሪ ክልል የመጡት ወይዘሮ በክሪያ እስማኤል ናቸው።
"ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ደረጃ ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ህብረትን ማጠናከርና በጋራ በርትቶ መስራት ይገባል" ይላሉ።
''ኢትዮጵያዊያን የሚበጀን እንደ ጥንቱና ድሮ እንደነበረው አንድ ለይ መሆን ነው'' ያሉት ወይዘሮ በክሪያ፤ ተጋግዞ ማደግ፣ መረዳዳትና በአንድነት መቆም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መገለጫ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “እኩልነትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በመከበር ላይ ይገኛል።