ቀጥታ፡

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተገኘው የምርት መጠን ዝቅተኛ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ሃምሌ 12/2010 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተገኘው የምርት መጠን ዝቅተኛ መሆኑ ተገለፀ። ምርቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገው የግብዓት አቅርቦትና የፋይናንስ እጥረቶች መሆናቸውን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጠቁሟል ። ኢንስቲትዩቱ በ2010 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀምና በ2011 በጀት ዓመት መነሻ መሪ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። የኢንስቲትዩቱ የእቅድ፣ ፖሊሲ ጥናትና መረጃ ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን አበበ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በበጀት አመቱ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሻለ አቅም ቢፈጠርም አፈፃፀሙ ግን ዝቅተኛ ነው። በበጀት ዓመቱ በዘርፉ በአዲስ መልክ 50 ቢሊዮን ብር የማምረት አቅም ያለው ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ አፈፃፀሙ 69 ቢሊዮን ብር የማምረት አቅም መድረሱ አንዱ ለተፈጠረው አቅም ማሳያ መሆኑን ነው ያስረዱት። በዚህም በዘንድሮው በጀት ዓመት 73 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ለማምረት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ እንዳልቻለ ነው ያመለከቱት። በዘንድሮው ዓመት የተመረተው ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ30 በመቶ ማሽቆልቆሉንም ነው ያስረዱት። ለዚህም የግብዓትና ኃይል እጥረቶች ኢንዱስትሪዎቹ ከ10 በመቶ በታች ባለ አቅም እንዲሰሩ ማስገደዱን በምክንያትነት የሚጠቀስ እንደሆነም ገልፀዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትና በአነስተኛ ሁኔታ ያለውም በአግባቡ ያለመደልደል ለምርት ማነሱ እንደምክንያት የሚቀመጥ መሆኑንም ነው ያመለከቱት። በአዲሱ በጀት ዓመት ችግሩን ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልጸው፤ የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታትም ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ለማቅረብ የሚያስችል ድርጅት ለማቋቋም የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም ጠቁመዋል። በበጀት ዓመቱ ለ1 ሺህ 715 የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች የቴክኒክና የማኔጅመንት አቅምን የሚያሳድጉ ስልጠናዎች መሰጠታቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም