በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ የታደሙ ዜጎች በአዲስ አበባ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ የታደሙ ዜጎች በአዲስ አበባ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ የታደሙ ዜጎች በአዲስ አበባ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።
15ተኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል።
ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን አስጎብኝተዋል።
በዚህም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና የሆነችው አዲስ አበባን የሚመጥኑና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የተጀመረውን የብልጽግና ጎዞ እውን ለማድረግና አገርን ለመገንባት ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንዳቸው ብሔራዊ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባልም ብለዋል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍሎች የተገኙት የበዓሉ ታዳሚዎች ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላት ቢኖሩም በህዝብና በመንግስት የተባበረ ክንድ ድል እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ከደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የመጡት ወይዘሮ ዛይዳ ግዛው "የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አገሪቷ ከገጠማት ችግር በመውጣት በድል ዋዜማ ላይ መከበሩ ታላቅ ያደርገዋል" ብለዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የመጡት የሰላም አምባሳደር ቁፋ ጎቤ በበኩላቸው፣ "አገሪቷ የተያያዘችውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል የህዝቦች አንድነትና የጋራ እሳቤ ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከደቡብ ኦሞ ዞን በመምጣት በበዓሉ ላይ የታደመው ወጣት ሰጎ ኤሪ በበኩሉ በተለይ ወጣቱ ከመንግስት ጋር በመሆን የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይኖርበታል ብሏል።
ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ የብር ብሔረሰብ ተወካዮቹ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት ዛሬ የመስቀል አደባባይ፣ የአንድነት ፓርክ እና የእንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል።