የህወሓት ጁንታ በዓለም ላይ የሚገኙ ሽብርተኛ ቡድኖች ከፈጸሙት በላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል... በአማራ ክልል የስራ ሃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ጁንታ በዓለም ላይ የሚገኙ ሽብርተኛ ቡድኖች ከፈጸሙት በላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል... በአማራ ክልል የስራ ሃላፊዎች
ባህር ዳር፤ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ )የህወሓት ጁንታ ቡድን በዓለም ላይ በሽብርተኝነት የተፈረጁት ቡድኖች ከፈጸሙት በላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸሙን የአማራ ክልል የተለያዩ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።
የህወሓት ቡድን በፈጸማቸው ዘግናኝና ጸያፍ ወንጀሎች በአሸባሪነት ሊጠየቅ ይገባል ሲሉም አመራሮቹ ገልጸዋል።
15ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ በባህርዳር በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ የስራ ላፊዎች ቡድኑ ከፖለቲካ ፓርቲነት እንዲሰረዝም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ፕሬዝዳንት ሻምበል ፈንታየ አወቀ ለኢዜአ እንደገለጹት የህወሓት ቡድን በዓለም ላይ የሚገኙ ሽብርተኛ ቡድኖች ከፈጸሙት በላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል።
"ቡድኑ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የተቃወሙትን ሃይሎች ሁሉ ያለበቂ ምክንያት በ24 ሰአት ውስጥ በአሸባሪነት በመፈረጅ ዜጎችን ማሰቃየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው" ሲሉ አስታውሰዋል።
ቡድኑ በማይካድራ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀልና በሌሎች ክልሎች የፈጠራቸው ግጭቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት በተኛበት በማጥቃት የሃገር ሃብት የሆነውን ትጥቅና ስንቅ የመዝረፍ እኩይ ተግባር መፈጸሙንም አመልከተዋል ።
"የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተሰምቶ የማይታወቅ የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው።
"ቡድኑ ንጹሃንን በጅምላ የጨፈጨፈ ነው" ያሉት ኅላፊው አሁንም እየወጡ ያሉ የፈጸማቸው ዘግናኝ ወንጀሎች ቡድኑን በአሸባሪነት የሚያስፈርጀው መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ህውሃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ያለመ በመሆኑ ጽንፈኛ ቡድኑ በአሸባሪነት ወንጀል ሊጠየቅና ከፖለቲካ መድረክ ሊወገድ ይገባል" ነው ያሉት።
ቡድኑ የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ አስከፊ በደሎችን ሲያደርስ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው።
"ህዝቡ ግን ትእግስት በማድረግ ቡድኑ ለጦርነት ያሰለፋቸው ቁስለኞችን እስከመንከባከብ ወገንተኝነቱን አሳይቷል" ብለዋል።