የህወሃት ጁንታ አባላትን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል….ፌዴራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ጁንታ አባላትን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል….ፌዴራል ፖሊስ
ጎንደር፤ህዳር 28/2013(ኢዜአ) በሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ላይም ሆነ በሲቪል ህብረተሰብ ላይ ግፍና በደል የፈጸመውን የህወሃት ጁንታ ለህግ የማቅረቡ ስራ በየደረጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ ተናገሩ።
በትግራይ ክልል የፌዴራል ተቋማትን የሚጠብቁ የፖሊስ አባላት በተፈጸመባቸው ግፍ ተባረው ጎንደር ከተማ የገቡ የፖሊስ አባላትን ዛሬ አወያይተዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የፌደራል ፖሊስ የኮማንዶ ሃይል መቀሌ በመግባት በአሁኑ ወቅት ከህግ ማስከበር ጎን ለጎን ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሰላማዊ ህዝቦችን ሲያሰቃይ የነበረው የህወሃት ጁንታ ቡድን አባላትና ተላላኪዎች ጭምር አንድ በአንድ ተለቅመው ለህግ እንዲቀርቡ የፖሊስ ኮማንዶ ሃይል ተልእኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ገልፀዋል።
ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረቡን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል የተሳካ ፖሊሳዊ ተግባር ለማከናወን እንዲቻል ተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ ሃይል ወደ ክልሉ ገብቶ እንደሚሰማራም ተናግረዋል።
ጁንታው ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ታሪክ ይቅር የማይለው የፖለቲካ ደባ መፈጸሙን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በሀገሪቱ በየትኛውም አካባቢ ለተፈጠሩ ግጭቶች ብሎም ለዜጎች መፈናቀልና ሞት የሴራው ባለቤት መሆኑን አብራርተዋል።
''የፌዴራል ፖሊስ አባላት በህወሃት ጁንታ ግፍና በደል ቢፈጸምባችሁም ዋጋ የከፈላችሁት ለህዝባችሁና ለህገ-መንግስታችሁ በመሆኑ ታላቅ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል'' ብለዋል፡፡
በወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በጥበቃ ተሰማርቶ የነበረው ዋና ሳጅን ተፈራ ንጉሴ “የህወሃት ጁንታ በሸረበው ሴራ ባላሰብነውና ባልጠበቅነው መንገድ ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጽሞብናል” ሲል ተናግሯል፡፡
“ተኩስ ከከፈተብን የትግራይ ልዩ ጋር ሃይል በጀግንነት ተዋግተን ተዋድቀናል” ያለው ዋና ሳጅን ተፈራ ''ጁንታውን ለህግ ለማቅረብ ዳግም ግዳጅ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ'' ብሏል፡፡
በአክሱም አየር ማረፊያ በጥበቃ ስራ ተሰማርቶ የነበረው ዋና ሳጅን ሙሉ ሸዋረጋ በበኩሉ “በውስጣችን የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የከሃዲው ጁንታ ተልዕኮ አስፈጻሚ የፖሊስ አባላት ታሪክ ይቅር የማይለው የክህደት ወንጀል ፈጽመውብናል ” ብሏል፡፡
“የትግራይ ልዩ ሃይል በፖሊስ መለያ ልብሳችን ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ ልብሳችንን አስወልቆ ለመቀማት የጠነሰሰውን ሴራ በማክሸፍ በእሳት አቃጥለነዋል” ሲል ተናግሯል፡፡
ዋና ሳጅን ሃብታሙ ታከለ በበኩሉ "በትግራይ ክልል የፌደራል ተቋማትን እንድንጠበቅ ግዳጅ ተሰጥቶን በነበርነው የፖሊስ አባላት ላይ በጨለማ ቤት በእስር ከማንገላታት ጀምሮ በውሃ ጥምና በረሃብ ቅጣት ተፈጽሞብናል” ብሏል፡፡
የፌደራል ፖሊስ አባላቱ በሰሜን ጎንደር ዞን የበየዳና የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የጎንደር ከተማ ህዝብ ባደረጉላቸው የክብር አቀባበልና እንክብካቤ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡