ከግለሰብ እስከ አገር የዘለቀ ጉዳት እያስከተለ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ከግለሰብ እስከ አገር የዘለቀ ጉዳት እያስከተለ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) ከግለሰብ እስከ አገር የዘለቀ ጉዳት እያስከተለ ያለውንፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሴቶችና ህፃናት ወጣቶች ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን “በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የማይታገስ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ እንዳሉት
በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የቀጠለ በመሆኑ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመለወጥ መስራት" እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃትን መከላከል ጊዜ የማይሰጠው እና ተገቢ ትኩረትን የሚፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሚደርሰው ጥቃት የሚያስከትለው ጉዳት ከግለሰብ እስከ አገር የዘለቀ በመሆኑ ይህን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር መስራችና ዳይሬክተር ማሪያ ሙኒር እንዳሉት ለሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እና ተደራሽነት እንዲኖር መስራት ይገባል።
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ጾታዊ ጥቃቶች በሚደርሱበት ጊዜ ወደ ህግ አግባብ የመሄድ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች መጠለያ ጥምረት አስተባባሪ ወይዘሮ ህሊና አጥላባቸው፤ ቀኑ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች የሚታወሱበት መሆኑን ገልጸዋል።
በኮቪድ ወቅት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት የተለያዩ አገልግሎትን ለሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና እና ሽልማት የሚሰጥበት ፕሮግራም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በዓለም ለ29ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።