የከፍተኛ ትምህርትን ውጤታማነት የሚያሻሽል የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ ተዘጋጅቷል...የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርትን ውጤታማነት የሚያሻሽል የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ ተዘጋጅቷል...የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
አዳማ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ ሰውን ከማፍራት ባለፈ ይበልጥ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ መዘጋጀቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቁ።
ነባሩ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ያለበትን ክፍተት ለመፍታትም በረቂቅ ደረጃ የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የፖሊሲ ማሻሻያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
በአዳማ ከተማ እየተካሔደ ባለው የዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂክ እቅድ የግምገማ መድረክ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት እንዲችሉ የሚመሩበት የዘርፍ ፖሊሲና ስትራተጂ ተዘጋጅቷል።
ተቋማቱ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራትም ባለፈ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን መርጦ በማምጣት ፣በማፍራትና በማላመድ ህብረተሰቡን ለማገልገል የሚያስችል ስራ እንዲያከናውኑ የሚያስችል የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተለይም በሳይንሱ ዘርፍ የዳበረ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እንዲኖር የተቋማቱን አቅም ማሳደግና ተልዕኮዋቸውን እንዲወጡ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንም ይሔንን ተረድተው እንደ የዩኒቨርሲቲዎቻቸው ነባራዊ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጓቸውን ስራዎች እንዲያከናውኑ እንደሚጠበቅም ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገልጸዋል።
በመድረኩ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታት ስራ የሚያደርጓቸው እቅዶች ላይ በመመካከርና ተሞክሮ በማዳበር የተሻለ እቅድ ይዘው እንዲወጡ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
"በነበረው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አሁን ሀገሪቷ የደረሰችበትን ልማትና እድገት ማስቀጠል አይቻልም" ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ፅሑፍ ያቀረቡት ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው።
ነባሩ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ሰፊ ክፍተት ያለበት ከመሆኑም ባለፈ የትምህርት ሴክተሩን ውስብስብ ችግር በአሰራርና አደራጃጀት ላይ በሚደረግ ለውጥ ብቻ መፍታት እንዳልተቻለም አመልክተዋል።
የውጭ ሀገር ተሞክሮዎችን ጭምር ባከተተ መልኩ ሁሉን አቀፍ ጥናትን ተደርጎበት በረቂቅ ደረጃ የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የፖሊሲ ማሻሻያ ሒደት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
እያጋጠሙ ያሉ ክፍተቶችን ከመሙላት አኳያም ቀደም ሲል 70/30 የነበረው የከፍተኛ ትምህርት የተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ የቅበላ መርሃ-ግብር እንዲቀር በማድረግ 55/45 እንዲሆን መደረጉን ጠቁመዋል።
"የተማሪዎች ዝቅተኛው የዩኒቨርሲቲ የቆይታ ጊዜም አራት ዓመት እንዲሆን ተደርጓል" ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮ በመለየትና የያዙትን ሰነዶች ፍተሻ በማድረግ ወደ ትግበራ እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።
"የተዘጋጀው ፖሊሲ፣ መሪ እቅድ፣ ስትራቴጂና የማስፈፀሚያ ፕሮግራሞችም የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ናቸው" ብለዋል።
በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ለሶሰት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ ከ46 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ፕሬዘዳንቶችና ምክትል ፕሬዘዳንቶችን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማትና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።