ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በዛሬው እለት ትምህርት ጀመሩ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የ2013 የትምህርት ዘመን በመንግስት ትምህርት ቤቶች ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህርት በይፋ ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመካኒሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ትምህርቱን በይፋ አስጀምረዋል።

አሁን ላይ ኮቪድን የመከላከል ግንዛቤው በማደጉና የግል ንጽህና መጠበቂያ የህክምና ግብአቶች በአገር ውስጥ መመረት በመቻሉ ትምህርት መጀመሩንም አንስተዋል።

የመማር ማስተማሩን ሂደት ምቹ ለማድረግ ተጨማሪ 2 ሺ 300 የመማሪያ እና 118 የመመገቢያ ክፍሎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፤ ላለፉት ስምንት ወራት በአማራጭ ቴክኖሎጂ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

ባለፉት 45 ቀናት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የክለሳ ትምህርት አጠናቀው ፈተና መውሰዳቸውንም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ለተማሪዎች የግል ንጽህና መጠበቂያ አስፈላጊ ግብአቶች በመሟላታቸው የገፅ ለገፅ ትምሀርት እንዲጀምሩ መደረጉንም ሃላፊው ተናግረዋል።

የትምህርት መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተማሪዎቹ የተዘጋጀውን ዩኒፎርም፣ ጫማ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች አበርክተዋል።

የተማሪ ወላጆችም ለልጆቻቸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

የኮቪድ 19 ተግዳሮትን በመቋቋምና ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት በመጀመሩ ምክትል ከንቲባዋ ለተማሪዎቹ የእንኳን አደረሳቸሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም