ቀጥታ፡

ለምርጫው የሚዘጋጀው የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል መተግበሪያ እየተጠናቀቀ ነው - ብሮድካስት ባለስልጣን

አዲስ አበባ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል እያበለፀገ ያለውን መተግበሪያ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ አብዮት ለሚታ ለኢዜአ እንደገለጹት መተግበሪያው ተሻሽሎ እየበለጸገ ያለው ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ከእጅ ንክኪ ነጻ ለማድረግ ነው።

መተግበሪያውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ ምርጫ ቦርድና ብሮድካስት ባለስልጣን በጋራ እያዘጋጁት መሆኑንም ተናግረዋል።

"የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መገናኛ ብዙሃንና የተመደበውን የአየር ሠዓት ወደ ሲስተሙ በማስገባት መተግበሪያው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ቀመር መሰረት ለእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲና ሚዲያ የተዘጋጀውን ሠዓት ይደለድላል" ብለዋል።

መተግበሪያው የሰው ጉልበት፣ ጊዜና ሀብት በመቆጠብ ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችና መገናኛ ብዙሀን በድልድሉ መሰረት መረጃቸውን በፍጥነት እንዲያገኙም ያደርጋል ተብሏል።

ቴክኖሎጂው መገናኛ ብዙሃን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ለማንና በየትኛው ሠዓት መስጠት እንዳለባቸው ጊዜ ሳይፈጁ ለማወቅ እንደሚያስችላቸውም ተገልጿል።

መተግበሪያው በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ጥቅም የዋለ ሲሆን አስፈላጊው ማሻያ ተደርጎ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ነው አቶ አብዮት የገለጹት።  

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ መተግበሪያው በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ጥቅም ላይ የዋለ ቢሆንም በወቅቱ በአጭር ጊዜና በችኮላ በመዘጋጀቱ ያልተካተቱ ክልሎችና ቋንቋዎች በማካተት እየተሻሻለ ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ ኒቆዲሞስ ጌታሁን መራጩ ሕዝብ በእውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ድምጹን እንዲሰጥ በመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል መመሪያ የተጠቀሱ ባለድርሻ አካላት ተናበው መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀመሩን ሲወስን 25 በመቶ የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ለሁሉም ፓርቲዎች በእኩል እንደሚደለደል በመመሪያው ተቀምጧል።

እያንዳንዱ ፓርቲ የሚያቀርበው የዕጩ ብዛት እንዲሁም የሴትና አካል ጉዳተኛ ዕጩ ብዛት ከግምት መግባት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት።

"ፓርቲዎቹ ቀደም ሲል በክልልና በፌዴራል ምክር ቤት ያላቸው የወንበር ብዛት ከግምት መግባት አለበት፣ ይህም ለቀመሩ ዋናው መሰረት መሆን እንዳለበት በመመሪያው ላይ ተመልክቷል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ቀመሮቹን መሰረት በማድረግ ቦርዱ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት እያበለጸገ ባለው መተግበሪያ የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ሰርቶ ያሳውቃል።

ቀደም ሲል በተካሄዱ ምርጫዎች የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል በእጅ ዕጣ በማውጣት ይከናወን እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም