የኦሮሚያ ግብርና ምርምር እና የቻይናው አፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩቶች በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ግብርና ምርምር እና የቻይናው አፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩቶች በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በቻይና የሳይንስ አካዳሚ ስር የሚገኘው አፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩት በግብርና ምርምር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና የቻይና አፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፋንግ ዩንቲንግ ናቸው የተፈራረሙት።
ተቋማቱ ስምምነቱን የፈረሙት በሳምንቱ መጨረሻ ሲሆን የግብርና ምርምርና የልማት ሥራዎችን እንዲሁም የአካባቢና ስነ-ምህዳር ምርምር በጋራ ለማካሄድ ተስማምተዋል።
በመስኩ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠት፣ የገንዘብ ድጋፍ በማፈላለግ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራ እንዲሁም የአካዳሚክና የባለሙያዎች ልውውጥ ማድረግ በስምምነቱ ተካተዋል።
ተቋማቱ በመግባቢያ ስምምነቱ የተለዩ የትብብር መስኮችን ለመፈጸም ይረዳ ዘንድ በቻይና ሻንዶንግ ግዛት ዌይፋንግ ከተማ አዲስ በተመሰረተው "ዌይፋንግ ሞደርን አግሪካልቸር ኤንድ ኢኮሎጂካል ኢንቫይሮመንት አካዳሚ" ግቢ የቻይና-ኢትዮጵያ የግብርናና አካባቢ የምርምር ማዕከል ለመመስረት እንዲሁም በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ማዕከል ለመክፈት መታቀዱ ተገልጿል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ "የግብርና ዘርፉን በምርምርና በኢንቨስትመንት መደገፍ የሚችሉ ጠንካራ አጋሮች ማግኘቱ መሰረታዊ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
የግብርና ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና ቀዳሚ እንደሆነ በተለይም ዘርፉ ከያዘው ሰፊ የሰው ኃይልና ለወጪ ንግድ ካለው ጠቀሜታ አንጻር ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት በተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ግብርና ትልቁን ድርሻ ቢወስድም ዘርፉን በማዘመን ፈጣን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማምጣት ባለመቻሉ አሁንም በዘርፉ የሚተዳደሩ ዜጎች ህይወት አለመሻሻሉን ጠቁመዋል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለግብርና ትኩረት በመስጠት ዘርፉን ለማልማት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደሩ መግለጻቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፋንግ ዩንቲንግ በበኩላቸው ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምርምሮችን በማካሄድ የግብርና ምርቶችን ማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
አነስተኛ ማሳ ላላቸው ገበሬዎች መስኖን በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ አሰራሮችን ለመዘርጋት፣ የግብርና ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ አነስተኛ ማሽነሪዎች በማምረት ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ እንዲሁም አሲዳማ አፈርን አክሞ ለምርታማነት ለማብቃት የሚያስችሉ ምርምሮች ለመከወን ፍላጎት መኖሩንም ገልጸዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ እንዲፈረም በሼንያንግ ከተማ በሚገኘው የቻይና ሳይንስ አካዳሚ የአፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩት በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ገሸሬ አብዲሳ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል።
የቤጂንግ የውጭ ቋንቋዎች ጥናት ዩኒቨርሲቲ በመስከረም 2013 ዓ.ም የአማርኛ ቋንቋን በቅድመ-ምረቃ መርሃ ግብር ማስተማር እንደሚጀምር መግለጹ የሚታወስ ነው።
በቻይና የሳይንስ አካዳሚ ስር የሚገኘው አፕላይድ ኢኮሎጂ ኢንስቲትዩት ቻይና በስነ-ምህዳር፣ በአካባቢና በተፈጥሮ ሀብት ምርምር ያላትን አቅም ማጠናከርን ዓላማ በማድረግ እ.አ.አ በ1954 የተቋቋመ ነው።
በ1994 ዓ.ም የተቋቋመው የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም በክልሉ የግብርና ልማትን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በድህነት ቅነሳ ሥራዎች አስተዋጽኦ የማድረግ ግብ ያለው ነው።