እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓትን በማስፈን ሃገራዊ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓትን በማስፈን ሃገራዊ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አርባ ምንጭ ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት በማስፈን ሀገራዊ ለውጡን ከድር ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ የጋሞ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።
“እኩልነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መርህ ቃል15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የጽህፈት ቤቱ የፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው አስራት እንደገለጹት የዘንድሮው በዓል በጁንታው ሽንፈት ማግስት መከበሩ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል።
"በማስመሰል ፖለቲካ ላይ የተመሠረተው ቡድን ከህዝቡ ጫንቃ ላይ ወርዶ ለሁሉም ዜጎች እፎይታን ፈጥሯል" ብለዋል።
"በተለይ ባለፉት 27 ዓመት የህወሃት አመራሮች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳሻቸው ሲበዘብዙ ከመቆየትም በላይ በህዝቡ መካከል ልዩነትና መጠራጠርን ሲፈጥሩ ቆይቷል" ሲሉም ተናግረዋል ።
የለውጡ መንግስት ቡድኑን በማስወገድ እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የህወሃት ጽንፈኛው ኃይል ብሔር ብሔረሰቦች ያቆዩትን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማደፍረስ ሴራ ሲያሴር መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የጋሞ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሪት ዓለሚቱ ዮሴፍ ናቸው።
በሀገራችን ለሚደረገው ሁለንተናዊ ዕድገት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ ሴቶች ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
"ሴቶች ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፋቸው መብቶች እንዲረጋገጡ በሀገራችን ምቹ መደላድል የፈጠረው ለውጥ እንዳይቀለበስ በትኩረት ይሠራል" ብለዋል።
የጋሞ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኮንን ቦራጎ "የመንግስት ሠራተኛው የህዝብ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ጁንታው ከፈጠረው ጠማማ አስተሳሰብ በመውጣት ከለውጡ ቁመና ጋር በመስተካከል ህዝቡን ከልብ ማገልገል ይገባል" ብለዋል።
በበዓሉ ላይ “የህወሓት ኢ-ህገመንግስታዊ እንቅስቃሴና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማዳን የተወሰዱ ተግባራት እንዲሁም ሀገራዊ ሪፎርም ለጠንካራ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።