ክፉ ቀን ያልበገረው ፍቅር--

107

ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት አባል ባለቤቷን ከህወሓት ጁንታ የታደገችው ለተብርሀን ገብረትንሳኤ ክፉ ቀን ላልበገረው ፍቅር ተምሳሌት ሆናለች።

ሃምሳ አለቃ ካሳሁን ረጋሳ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ውስጥ በሕክምና ዘርፍ ከ11 ዓመት በፊት ነው ማገልገል የጀመረው።

ታሪኩ እንዲህ ነው:-

ሃምሳ አለቃ ካሳሁን ለተብርሀን ገብረትንሳኤ ከምትባል ከሰሜን ኢትዮጵያ ከተገኘች መልከ መልካምና ፍልቅልቅ ወጣት ጋር ከ8 ዓመታት በፊት ጎጆ ቀልሶ ኑሮ መስርተዋል።

በትዳር ዘመናቸው አንድ ልጅ አፍርተው ኑሯቸውን በፍቅር ሲመሩ እንደነበር ያስታውሳል፤ ሃምሳ አለቃ ካሳሁን አሁን ከሠራዊቱ ጋር ተገናኝቶ በአክሱም ከተማ ግዳጁን በመወጣት ላይ ይገኛል።

ሃምሳ አለቃ ካሳሁን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም የአካባቢው ተወላጅ በሆነችው ባለቤቱ ለተብርሃን አማካኝነት የጥቃቱ ሰለባ ከመሆን ተርፏል።

ቀድሞም አሁን የጁንታው አባላት በሆኑ ጥቂት የሠራዊቱ አመራሮች ተጽዕኖ ይደርስበት እንደነበረ የሚናገረው ሃምሳ አለቃ ካሳሁን ከባለቤቱ ጋር በመሆን የሚጠነስሱበትን ሴራ በብልሀት በማለፍ መቆየቱን ይገልፃል።

ጁንታው ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንደከፈተ ባለቤቷ ጉዳት እንዳይደርስበት ያሰበችው ለተብርሀን ስንቁን አስይዛ ለጥቂት ጊዜ ወደ ጫካ እንዲያመልጥ ማድረጓን እንዲህ ይገልጻል።

በጫካ ተደብቆ በቆየባቸው ቀናት የሚበላውና የሚጠጣውን ይዛ በመሄድ ታጽናናው እንደነበረም ይናገራል።

በአጥፊው ቡድን ይደርስበት ከነበረው አደጋ ከታደገችው ባለቤቱ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖር እንደነበረም ያስታውሳል።

ባለቤቱና ልጁ ሽራሮ ከተማ እንደሚገኙ የሚናገረው ሃም አለቃ ካሳሁን ምናልባትም ስለ እሱ ደሕንነት በጭንቀት ውስጥ እንደሚሆኑ ያስባል።

ቤተሰቦቹ ያሉበትን ሁኔታ የማያውቀው ሃምሳ አለቃ ካሳሁን የባለቤቱና የልጁ ደህንነት ተጠብቆ እንዲቆዩ በመመኘት ድሉ የጀግናው መከላከያ ሠራዊት በመሆኑ ደስታውን ገልጿል።

የሠራዊት አባል የሆነውን ባለቤቷን ሃምሳ አለቃ ካሳሁን ረጋሳን የታደገችው ለተብርሃን ገብረትንሳኤ ክፉ ቀን ላልበገረው ፍቅር ተምሳሌት ሆናለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም