ቀጥታ፡

ኢትዮ-ኤሌትሪክ ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር እንደማይሳተፍ ገለጸ

አዲስ አበባ ሀምሌ 12/2010 የኢትዮ-ኤሌትሪክ ስፖርት ክለብ  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር እንደማይሳተፍ አስታወቀ። በፕሪሚየር ሊጉ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት የመጨረሻ ጨዋታ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በውድድሩ እንደማይሳተፍ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 30ኛ ሳምንት ጨዋታ በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 63ኛው ደቂቃ ላይ በከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጦ የቀረው 27 ደቂቃ  በቀጣዩ ቀን እንዲካሄድ ተደርጓል። ጨዋታው ሲቋረጥ ውጤቱ ዜሮ ለዜሮ ነበር። በዚህም መሰረት ሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም ተቋርጦ የነበረው ጨዋታ ድጋሜ ከቆመበት ሲቀጥል ድሬዳዋ ከተማ በዳኛቸው በቀለ ሁለት ጎሎች ወልዋሎን ሁለት ለባዶ በማሸነፉ ድሬዳዋ ከመውረድ ሲተርፍ በአንጻሩ ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል። የኢትዮ-ኤሌትሪክ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሰ ኩሳ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በሜዳው ከመከላከያ ውጭ በማንም ክለብ ተሸንፎ እንደማያውቅ ያነሳሉ። በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አንድም ጨዋታ ከሜዳው ውጪ አሸንፎ እንደማያውቅም ተናግረዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲቋረጥ ኢትዮ-ኤሌትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ሁለት ለዜሮ እየመራ እንደነበር አስታውዋል። ቡድኖቹ በዕለቱ በተመሳሳይ ሰዓት የተጫወቱበት ዋነኛው ምክንያት እየታወቀ የወልዋሎና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ተቋርጦ በቀጣዩ ቀን መካሄዱ አግባብነት የሌለው ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል። በያዝነው ዓመት ብዙ ጨዋታዎች ከባድ ዝናብ እየዘነበ ሳይቋረጡ ሙሉ ጨዋታው እንደሚጠናቀቅ ገልጸው የወልዋሎና የድሬዳዋ ጨዋታ መቋረጡ "ፍትሐዊ ካለመሆኑ በላይ የሌላኛውን ጨዋታ መረጃ በማሳባሰብ የነበራቸውን ውጤት በችሎታ ሳይሆን በመላቀቅ ለማስቀየር መደረጉ የተፈጸመው ድርጊት ድብቅ ተልዕኮ እንዳለው በግልጽ ያሳያል" ብለዋል። በቀጣይ ቀን በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ "ድሬዳዋዎች ወደ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ የግብ ክልል በቀላሉ በመድረስ  ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል" ነው ያሉት አቶ ለገሰ። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጨዋታው ሲካሄድ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል በገለልተኛ አካል ታይቶና አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ውሳኔ እስከሚሰጥ በጥሎ ማለፍ ውድድሩ እንደማይሳተፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማሳወቁን ገልጸዋል። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በአንፃሩ በጥሎ ማለፍ ውድድሩ መሳተፍ እንዳላባቸው ለክለቡ ማሳወቁን የጠቀሱት አቶ ለገሰ፤ የፌዴሬሽኑ ምላሽ ፍትሐዊ  አይደለም ብለዋል። በዚህም ምክንያት ላቀረብነው ጥያቄ ፍትሐዊ ምላሽ ካላገኘን በውድድሩ ላይ እንሳተፍም በሚል ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በሰበታ ስታዲየም ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከጅማ አባ ጅፋር በጥሎ ማለፍ ውድድር የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርሃ ግብር አውጥቶ ነበር። የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ኢትዮ-ኤሌትሪክ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በ35 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም