ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ይዞ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

ህዳር 28/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ይዞ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ገለጸ።

ግለሰቡ ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፓትሮል ስራ ላይ በነበሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል አባላት በቁጥጥር እንዳዋሉት ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጸጥታና ህግ ማስከበር የቀጠና ሁለት አዛዥ ኮማንደር ባደግ ክፍሌ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ልውል መቻሉን ገልጸዋል።

በሰዓቱ ይዞት በነበረው ሻንጣ ፍተሻ ሲደረግ በርካታ ሐሰተኛ የደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ኖቶችና በተለያዩ የሂሳብ ደብተሮች ላይ ከ184 ሺህ ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ተገኝቶበታል፡፡

ግለሰቡ በፖሊስ ሲጠየቅ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጀም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱንና ሐሰተኛ የደቡብ አፍሪካ ገንዘቦቹን ከሌላ ሰው በ57 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መግዛቱን የተናገረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ኮማንደር ባደግ ጠቁመዋል፡፡

ማንኛውም ሰው ከእንደዚህ አይነቱ ህገ ወጥ ተግባር እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ፣ ጥቆማ በመስጠትና መሰል ህገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመግለጽ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም