የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለሆነችው አዲስ አበባ እድገት የብሄር ብሄረሰቦች ርብርብ ያሻል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለሆነችው አዲስ አበባ እድገት የብሄር ብሄረሰቦች ርብርብ ያሻል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/2013 ( ኢዜአ) አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ በመሆኗ ለዕድገቷም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ትብብርና ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የተወጣጡ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች በአዲስ አበባ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም የተጠናቀቁና በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን አስመልክተው ለጎብኚዎቹ በመስቀል አደባባይ በስክሪን የታገዘ ገለጻ አድርገዋል።
አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ መሆኗንና ለእድገቷም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ትብብርና ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካትም በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ጉብኝቱ ለ15ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮቹ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ጉበኝታቸውን አጠናቀው በአንድነት ፓርክ ጉብኝት ላይ ናቸው።
ከሠዓት በኋላም የእንጦጦ ፓርክን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ነገ "እኩልነትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።