ቀጥታ፡

በስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስት ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠየቁ

ህዳር 28/ 2013 (ኢዜአ) በስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መንግስት የህወሃት ቡድን ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ከህግ ማስከበር በኋላ ባለው የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ምዕራፍ ዙሪያ የበይነ-መረብ ውይይቶች ያካሄዱ ሲሆን የአቋም መግለጫም አውጥተዋል።

በመግለጫቸው በእብሪት የተሞላው የሕወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው የክህደት ጠባሳ ጥሏል ነው ያሉት።

ቡድኑ የፈፀመውን ክህደት አጥበቀው እንደሚያወግዙ ገልጸው፤በአሁኑ ሰዓት መንግስት እያደረገ ያለውን አጠቃላይ የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ስራ እንደሚደግፉ ነው የገለጹት።

ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ኢትዮጵያን እና የአፍሪቃ ቀንድን በሽብር ሲያተራምስ የኖረውን የሕወሃት ቡድን መንግስት በሽብርተኝነት እንዲፈርጅ እና በሕዝብ ላይ ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት ለፈፀማቸው ወንጀሎች በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

እብሪተኛውና አረመኔው የሕወሃት ቡድን የማይ ካድራ ነዋሪዎችን በመታወቂያ እየለየ በዱላ በድንጋይ በገጀራና በመሳሰሉት በመጨፍጨፍና በገመድ ጭምር በማነቅ ከስምንት መቶ በላይ በሆኑ ወገኖች ላይ ያካሄደውን ጭፍጨፋ አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የማይካድራን ጨፍጫፊዎች የገቡበት ገብቶ በማደን ለሕግ እንዲያቀርብ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጥኚዎችን ስፍራው ድረስ በመላክ በተጨባጭ ማስረጃ ወንጀሉን እና የወንጀሉን ፈፃሚዎች በመለየት ላቀረቡት ፈጣን ሪፖርትም አመስግነዋል።

እብሪተኛውና አረመኔው የሕወሃት ቡድን ለራሱ ስልጣንና የሃብት ዘረፋ ለማመቻቸት ሲል በሀገር መከላከያ ላይ ጦርነት ማወጁን ገልጸዋል።

ቡድኑ የለኮሰው ጦርነት እራሱን መልሶ ሲለበልበው ጎረቤት ሃገራትን ወደ ግጭት ስቦ ለማስገባትና ምስራቅ አፍሪቃን የጦርነትና ሽብር ቀጠና ለማድረግ ሞክሯልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያኑ የኤርትራ መንግስት ምንም እንኩዋን ለተፈፀመበት ጥቃት አፀፋውን የመመለስ መብት ቢኖረውም የሕወሃት ትንኮሳ ቀጠናዊ ግጭት ለመቀስቀስ መሆኑን በመረዳት አፀፋ እርምጃ ላለመውሰድ በመወሰኑ አድንቀዋል።

የስዊዘርላንድ መንግስትና በስዊዘርላንድ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ኮምዩኒቲ አባላት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለችው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ መሳካት ለኢትዮጵያ ፣ለምስራቅ አፍሪቃና ለመላው የቀጠናው ሃገራት ሰላም ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት ከኢትዮጵያ መንግስት ቆን በመቆም ለሰላምና ለሕግ የበላይነት መከበር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በዚህ የበይነ መረብ ውይይት ላይ በጄኔቭ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ መገኘታቸውን ኢዜአ ከኢምባሲው ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም