ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የገጽ ለገጽ ትምህርት ጀመረ

ሆሳዕና፣ ህዳር 27/2013(ኢዜአ) የዋቸሞ ዩንቨርስቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የገጽ ለገጽ ትምህርት መጀመሩን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ እንደተናገሩት በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማስጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ከሶስት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ተመራቂ ተማሪዎችን በመቀበል ወደ ስራ ተገብቷል።

“ቀደም ሲል ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት የህወሀት ጽንፈኛ ቡድን ሀገሪቱን ትርምስ ውስጥ ለማስገባት ያደረገው ሙከራ የትምህርት መጀመሪያ ጊዜውን አስተጓጉሏል” ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት ተመራቂዎችን ለመቀበል እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተማሪዎች ህብረት ጋር ሲሰራ በመቆየቱም ባካሔዳቸው ውይይቶች ከጸጥታ ችግር ነጻ በማድረግ ስራው መጀመሩን ገልጸው ተማሪዎችም ከማንኛውም አሉታዊ እንቅስቃሴ በመጠንቀቅ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ በበኩላቸው ዩንቨርሲቲው የገጽ ለገጽ ትምህርቱ እንዲቋረጥ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቢሆንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የገጽ ለገጽ ትምህርቱን ለማስቀጠል በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተቀመጠው ፕሮቶኮል መሟላቱን ጠቁመዋል።

“ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት በመጠበቅና በሀገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የትምህርት ስራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል” ብለዋል።

የአምስተኛ አመት ሲቪል ምህንድስና ተማሪ የሆነችው አበበች ገብረኪዳን ለኢዜአ እንዳለችው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ስራ በመጀመሩ ደስተኛ ነች።

ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም ለመመረቅ መጓጓቷን የተናገረችው ተማሪዋ ቀዳሚ ትኩረቷም በተቀመጠው ጊዜ ትምህርቷን በማጠናቀቅ ህልሟን ማሳካት እንደሆነ ተናግራለች።

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ የገጽ ለገጽ ትምህርት የጀመረው ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዙር የተቀበላቸውን ከሶስት ሺህ 200 የሚበልጡ ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተምሮ እንደሚያስመርቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም