ስፖርት ለአንድነት እና ሰላም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት ለአንድነት እና ሰላም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2013 (ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ስፖርት ለአንድነት እና ሰላም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ተናገሩ።
የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እያካሄደ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ በሪፋንና እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመክፍቻ ንግግራቸው “ጉባኤው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በመካሄዱ ትልቅ ደስታና ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊና አህጉራዊ የሆኑ ሁለገብ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና የምትጫወት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
"አህጉራዊ አንድነትን ማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን የጋራ ዓላማ ለማሳካት ጠቀሜታ አለው" ሲሉም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።
ለዚህም የአፍሪካ ብሔራዊ የኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኀበር የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።
"ለአንድነትና ለሰላም ስፖርት አይነተኛ መፍትሄ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ለስፖርት ሁሉም የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንቷ ጉባኤው የተሳካና ፍሬያማ እንዲሆን በመመኘት ተሳታፊዎችም አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን መድረክ እንድታዘጋጅ የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ለሰጠው እድል ምስጋና አቅርበዋል።
"የአፍሪካ ስፖርት ያለ ሀገር መሪዎች ተሳትፎ የትም አይደርስምና የመሪዎች ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው" ሲሉም ጠይቀዋል።