"ጭካኔያቸው ምንም መለኪያ የለውም"' - ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ገዳሙ

161

አየለ ያረጋል - ኢዜአ

በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ አገር ሃሮማያ አካባቢ ተወለዱ። ከአባታቸው ሻምበል ገዳሙ ካሳዬ የወረሱትን የውትድርና ሙያ በ1946 ነበር አሀዱ ብለው የጀመሩት። በውትድርና ህይወታቸው በእግረኛ ወታደርነት፣ የመድፍ ምድብተኛ በመሆን ከዚያም ሃምሳ አለቃ ሆነው በኋላም በጦር መኮንንነት ከምክትል መቶ አለቃ እስከ ሜጀር ጄኔራል ማዕረግ ደርሰዋል። በ18ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንን ሆነው በገነት ጦር ትምህርት ቤት እንዲሁም በሀገረ-አሜሪካ በመድፈኛነትና በመገናኛ ወታደራዊ ጥበብ ተምረዋል። 

ከቅድመ 1953 መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ የደርግ መንግሥት አስከወደቀበት 1983 ዓ.ም ድረስ በሰራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች በኃላፊነት ሰርተዋል። በሁለተኛና አራተኛ መድፈኛ ሻለቃ አዛዥነት፣ በምድር ጦር መምሪያ መኮንንነት፣ በማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥነት፣ በቀድሞው አንበሳ 3ኛ ክፍለ ጦር የኋላው የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ እንዲሁም በአንደኛ አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የበረራ ደህንነት ጥበቃ ኃላፊነትም ሰርተዋል። በዚሁ ሙያም በተለያዩ አገራት ተዘዋውረው አገራቸውን አገልግለዋል።

ከሁመራ ገስጥ ዘመቻ እስከ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ወረራ በካራማራና ቆሬ ዐውደ ውጊያዎች አዝማች ነበሩ። በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመነ መንግሥታት በጦር ሰራዊቱ ለ38 ዓመታት አገልግለዋል- ሜጀር ጀኔራል ጌተቸው፤ ኢህአዴግ አገሪቷን ሲቆጣጠር ለ11 ዓመት ከመንፈቅ በአዲስ አበባው አለም በቃኝና በሐረር ማረሚያ ቤቶች ቆይተዋል። ኋላም ታስረው በተከሰሱበት ወንጀል በነጻ ከተሰናበቱ በኋላ በግል ሥራ ተሰማርተው ነበር። 

የዛሬው የ85 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ሜጀር ጀኔራል ጌታቸው ያለፉባቸውን የራሳቸው የቀድሞ ታሪኮች ጨምሮ በምድር ጦር ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍት እያበረከቱ ሲሆን፣ እስካሁንም አራት  መፃሕፍትን ለሕትመት አብቅተዋል። አሁንም ለሕትመት የተዘጋጀ መጽሐፍ አላቸው።

እኚህ የቀድሞ ጦር መኮንንና የታሪክ ፀሐፊ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። እነሆ ሃሳባቸው!!

በቀድሞ ጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሎትዎን ቢያጫውቱን?

አባቴ ወታደር ነበር። እኔም በወታደሮች ካምፕ ውስጥ ከወታደር ህብረተሰብ ጋር ነው ያደግኩት። በ1946 ዓ.ም ትምህርቴን አቋርጨ ውትድርና ገባሁ። ከተራ ወታደር ጀምሬ እስከ 50 አለቃ ደረስኩ። 18ኛው ዕጩ መኮንን ሆኜ በገነት ጦር ትምህርት ቤት ገባሁ። አባቴም መድፈኛ ነበር፤ እኔም በመድፈኛ ክፍል ገባሁ። በከባድ መሳሪያዎች ጥገና ተማርኩ። አገልግሎቴም በመድፈኛ ክፍል ነበር። በምክትል መቶ አለቃነት በአስተዳደር ኃላፊዎች አጋዥነት በተለያዩ የአስተዳደር ክፍሎች ስስራ ቆየሁ። በ1953 ዓ.ም ሶማሊያ በዳኖት ውጊያ ከፍታ ስለነበር ከአዲስ አበባ ወደ ምስራቅ ተዛወርኩ። በዳኖት ውጊያ ቢሳበብም፤ እኔ የነበርኩበት 4ኛ መድፈኛ ሻለቃ በ1953ቱ የእነ መንግሥቱ ነዋይ መፈንቀለ መንግሥት ተጠርጥሮ ስለነበር መጀመሪያ መኮንኖች ወደ አዲግራትና ሐረር እንዲሄዱ ተደረገ። ቀጥሎም ሙሉ ሻለቃው ለልምምድ ተብሎ ወደ ጅማ እንዲሄድ ሲደረግ እኔም ወደ ምስራቅ ዕዝ ተዛወርኩ።

በጄኔራል አማን ስር ካለው ምስራቅ ዕዝ 2ኛ ሻለቃ እያለሁ እንደገና ወደ ምድር ጦር መድፈኛ መምሪያ ተዛወርኩ። ቀጥሎም ወደ አሜሪካ ለትምህርት ተልኬ በመገናኛ መድፈኛ ሁለት ትምህርቶች ተምሬ ወደ አገር ቤት ተመለስኩ። ጅማ 4ኛ መድፈኛ ሻለቃ ተመደብኩ። እንደገና ወደ ምድር ጦር ዘመቻ መምሪያ መኮንን ሆኜ ተመደብኩ። ቀጥሎ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደህንነት ጥበቃነት በኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም ተመልምዬ በመጀመሪያ በአስተዳደር ቀጥሎም በሕንድ አገር ለሰባት ወራት የበረራ ደህንነት ጥበቃ ክፍል ሰርቻለሁ።

በ1966 ዓ.ም መንግስት ሲገለበጥ ከበረራ ደህንነት ወደ 4ኛ መድፈኛ ሻለቃ አዛዥነት ተመድቤ ድሬዳዋ ተዛወርኩ። በ1969 ዓ.ም ከድሬዳዋ ተነስቼ ወደ ሁመራ ‘ገስጥ ዘመቻ’ ሄድኩ። እንደገና ሶማሊያ ወረራ ስትፈጽም ወደ ምስራቅ ተመለስኩ። እኛ ስንደርስ ጠላት ጅግጅጋን ተቆጣጥሮ ስለነበር ካራማራ ላይ ደረስኩ። ጦሩ ጥሩ አመራር አልነበረውምና ወደ ቆሬ አፈገፈግን። ቆሬን መሰረትን እኔና ሜጀር ጀኔራል ወጋየሁ ጋሻው ነን።

ቀጥሎ ሳልታመም ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ተጠራሁ። ምሥራቅ ጀርመን ሄጄ ለአገራቸው ሲዋጉ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ የጦር ቁስለኞችን አሳክሜ ተመለስኩ። ወደ ምድር ጦር አስተዳደር መኮንን ተመደብኩ። ቀጥሎ የምስራቅ ዕዝ በኋላ /አንደኛ አብዮታዊ ሰራዊት የተባለው/ ምክትል አዛዥ ሆኜ በጀኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ በጀኔራል ውብሸት ደሴ፣ በጀኔራል ብርሃኑ ጀምበሬ ሥር ቆዬሁ። ቀጥሎም በዋና አዛዥነት ተሾምኩ።

በመጨረሻ መንግሥቱ ኃይለማርያም መጥተው ጎንደርና ጎጃምን ጠላት ተቆጣጥሮት ስለነበር 'ቴዎድሮስ ግብረ ኃይል የሚባል ጦር እየመራህ ጠላትን ከጎንደርና ጎጃም አጥፍተህ ጎንደር ላይ 5ኛ አብዮታዊ ሰራዊት ታቋቁማለህ' ተባልኩ። በምንም ተዓምር ሊሆን የማይችል ዕቅድ ነበር። የተጠናከረ ጦርም አልነበረም። መድፍና ታንክም የሌለው ጦር ይዤ ወለጋን ሳይቀር የተቆጣጠረ ጠላት እንድዋጋ አቅጣጫ ተሰጠኝ። ጦር ይመጣልሃል ተብዬ ሰንቀሌ /አምቦ/ በኋላም ጊንጪ ስጠባበቅ ይላክልሃል የተባው ጦርም ሳይላክ ቆየ፤ አሻጥር ሲሰራብኝ ነበር። በመጨረሻም ያለኝን ጥቂት ጦር አስረክቤ ቤት እንድቀመጥ ተደረገ። መንግሥቱ ኃይለማርያምም ከአገር ወጡ። ሐረር ወደ ቤተሰቦቼ ሄድኩ። በመጨረሻም የራሴ ጦር /ከወያኔ ጋር የተመሳጠሩ አመራሮች/ ለወያኔ አስረክቦኝ ታሰርኩ። ከ11 ዓመት በላይ ታስሬ ወጣሁ።

ሕወሃት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው የጭካኔ ጥቃት ምን ይላሉ?

ያልታረሙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ 27 ዓመት ቆይተው ሊሻሻሉ ያልቻሉ፤ ከክፉ ልባቸው ሊለወጡ ያልቻሉ ክፉዎች ናቸው። እባብ እንኳን ቆይቶ ሰንኮፉን ይቀይራል። በእኛ ሠራዊት ላይ የፈጸሙትን የጭካኔ ተግባር በዚህ ሠራዊት ላይ ፈጽመዋል። እንዲያውም ከዚያ የባሰ ነው። አብሯቸው የኖረ፤ ሬሽን አብራቸው ሲቆርስ የነበረን ሠራዊትን ነው የገደሉት። ጭካኔያቸው ምንም መለኪያ የለውም።

በቀድሞ ጦር ላይ የፈጸሟቸው የጭካኔ ተግባራት ምንድን ናቸው?

ወያኔ ከመሰረቱ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የለውም። ኢትዮጵያን የማፈራረስ እቅድ እንደነበረው ከመጀመሪያው ይታወቃል። የቀድሞ ሰራዊትን ይዞ የሚፈልገውን ዕኩይ ዓላማ ማሳካት ስለማይችል ነው ያፈረሰው። የሂትለር ጦር እንደተሸነፈ ጀርመኖች ጦሩን አልበተኑትም። ከአዲሱ ጦር ጋር መስራት የምትፈልጉ በዚህ፤ ወደ ራሳችሁ ሥራ መሄድ የምትፈልጉ በዚህ ብለው በየፍላጎታቸው በክብር ነው የሸኟቸው። ሂትለር ጦር ተብሎ በዓለም ላይ የሚወገዝ ሰራዊት ይህ እድል ኖሮት ለአገሩ ዳር ድንበር፣ ለውስጥ ጸጥታ ያልሆነው፣ ያልወደቀበት ያልተሰዋበት ቦታ የሌለው አልፎ ተርፎም በኮሪያ፣ በኮንጎ በዓለም አቀፍ ዘመቻዎችን ያደረገ ሰራዊት ሊበተን አይገባውም ነበር። 50 ዓመት የተለፋበት፣ ከድሃ ህዝብ ላይ ተነጥቆ 50 ዓመት የተገነባ ሰራዊት ነበር። በአንድ ጀምበር ሰራዊት አይገነባም።

ሰራዊቱ ይበተን ቢባል እንኳን መብታቸውን ጠብቆ ነበር ማሰናበት ያለበት። ጡረታ መብት ከልክሎ፣ ሕክምና ከልክሎ፣ እሱም ይቅር የዕድር ገንዘብ ነበረው ሰራዊቱ። ለመንግሥት የሚከፍለው ደሞዙ እስኪደርስም ይሁን ትንሽ ገንዘብ ለሀዘንተኛው ማስተዛዘኛ ገንዘብ ነበረው ይህንንም የከለከሉት ከጥላቻቸው ብዛት ነው። ጦሩን መበተን ብቻ አይደለም በህጻናት ላይ የፈጸሙት ግን ቀላል አይደለም። ከዝዋይ ህጻናት አምባ ግራ ቀኝ የማያውቁ ህጻናትን አስወጥቶ ለጅብ የሰጣቸው አሉ፤ ለጎረምሳ ችግር ውስጥ የከተታቸው አሉ። ለከብት እረኛ እያለ የወሰዳቸው አሉ። እስካሁን የት እንዳሉ የማይታወቁ። ያን የመሰለ ጭካኔ የሰራ መንግሥት ነው። መንግሥት ልበለውእንደገና እጅ እግር የሌላቸውን በሰው ሰራሽ መሳሪያዎች ብቻ መንቀሳቀስ የሚችሉ የጦር አካል ጉዳተኞች ከደብረ ዘይት የጀግኖች አምባ  አስወጥቶ ሜዳ ላይ ጥሏቸዋል። እነዚህንም በጭካኔ ነው የበተናቸው። በህጻናት ላይ ጭካኔ የፈጸመ ቂመኛ ነው። ትልቅ በደል ነው የፈጸመብን። በቀድሞ ሰራዊት ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ አመራር አድሎ ተፈጽሟል። ይሄ በእኔ ላይ ደርሶብኛል። እኔ ዘግይቼ ስለወጣሁ በጦር ኃይሎች የመታከም እድል አግኝቻለሁ። አንድ ወቅት ታምሜ ሆስፒታል እንድተኛ በሐኪሞች ተነገሮኝ ደረጃዬ /ጄኔራልነት/ በሚፈቅደው አገልግሎት እንዳገኝ ተጠይቆ ‘ይህ የደርግ ጀኔራል ከእኛ ጋር እኩል አይተኛም’ ተባልኩ። ከዚህ የባሰ መድሎ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ምን ተፈጸመ?

የህወሓት ጦር መኮንኖች ዘረፋ ከቀድሞ ጦር መኮንኖች አንጻር እንዴት ያዩታል?

አይይይ! ልዩነት ስትለኝ ይገርመኛል። እንዲህ ያለ ዘረፋ በኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመን እንኳን በወታደር ቤት ቀርቶ በሲቪል አላየንም። አላየንም። ሙልጭ አድርገው ነውኮ አገሪቷን ገፈው የወሰዱት። ሰሞኑን ስንት ሚሊዮን ፓውንድ ነው ሱዳን ወስጥ ከአንድ ወታደር አዛዥ ተያዘ የተባለውከየት መጣ ያ ሁሉ ገንዘብከዚህ ድሃ ህዝብ ላይ ነው። እኔ በአዛዥነት ቦታ ኖሬያለሁ። ገንዘብ በዓይኔ አይቼ አላውቅም። የሚታዘዝ ነገር ካለም እኔጋ አልፎ ከመጣ በወረቀት ነው የማየው። ለሚታዘዘው ነገርም ግልባጭ ለኦዲተር ይላካል። የኔ ልጅ በእኛ ጊዜ የውሎ አበል የለንም። በነጻ ነው የምናገለግለው። በሶ በጥብጡልን ብለን ሚሊሻውን በሶ እያስበጠበጥን ነበር አገሪቷን የምንጠብቀው። እና ዘረፋውንማ ከምን ጋር ታነጻጽረዋለህ። መለኪያም ይሄ ነው ብለህ ልታወጣለት አትችልም።

መንግሥት እየወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ምን ይላሉ?

የሰሜን ዕዝኮ ኢትዮጵያን የሚጠብቅ ነው። ጥበቃህን አንዱ ቢመታብህ ዝም ትለዋለህ? እሱ ተነካ ማለትኮ አንተ ተነካህ ማለት ነው። ያም ሰራዊት ተነካ ማለትም አንተ ተነካህ፤ ሀገር ተጎዳ ማለት ነው። ስለዚህ ትክክለኛ እርምጃ ነው የተወሰደው። ያለ ወታደር አገር አይኖርም። እንኳንም ዛሬ ዓለም በተወሳሰበችበት፤ አንዱ አንዱን ለማጥቃት በሚፈልግበት ጊዜ ቀርቶ ከጥንትም ወታደር ያስፈልግ ነበር።

የህወሓት ቡድን ለፈጸማቸው ግፎች ሕጋዊ ተጠያቂነት በተመለከተ የሚሉት ይኖራል?

ለእነዚህ ርህራሄ ይገባቸዋል? በፍጹም አይገባቸውም! ሰይጣን እንኳን ከሰዎች ላይ ዝም ብሎ አይወጣም። ቀስ እያለ አንተ 'ላላ' ስትል ነው የሚይዝህ። ሰይጣን ፈሪ ነው። እነዚህ ከሰይጣን የባሱ ጨካኞች ናቸው። በሠራዊቱ ላይ የፈጸሙት ግፍ አረመኔያዊ ነው።

በእውነቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእግዚአብሄር ሰው ናቸው። ተጠያቂነት በሕግ መሰረት መሆኑ ጥሩ ነው። ባለፈው አቶ በረከት ስምዖን እጄ ላይ ሰንሰለት አስረውብኛል ሲል ሰማሁት/በፈገግታ/ እኔን ከአዲስ አበባ በካቴና እጄን አስረው ነው በመኪና ሐረር ወስደው ያሰሩኝ። የታሰርኩበትን ክሴን ያወኩት ከስምንት ዓመት በኋላ ነው። ከዛ በኋላም እንደገና ለአራት ዓመታት ፍርድ ቤት ስመላለስ ነው የከረምኩት። የእነ በረከት ክስ በስንት ጊዜ ነው ያለቀውእንደዚህ መሆኑ ጥሩ ነው ለማስተማሪያ። ግን የነዚህ ሰዎች ፍርድ መታየት ያለበት በአገር ውስጥ ከሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን፤ በጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ነው። ወይም በሄግ /በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት/ ተላልፈው መሰጠት አለባቸው። በተገቢ ደረጃ ቅጣት እንዲያገኛቸው። ምናልባት በዓለም አቀፉ ሕግ አንዳንዴ ቅጥ ስለሚያጣ ራሳችን ፍርዳቸውን መስጠት ነው ያለብን። ለመሆኑ በእነሱ ያለቀው ሕዝብ ቁጥር ይታወቃልአሁንም በእነሱ ሰበብ እየሞተ ነው።

በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖራል ጄኔራል?

ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ብዙ ጠላት ነው ያላት። አንድም ወዳጅ የላትም። ምናልባት የተሻለች ጎረቤት ያለችን ኬንያ ናት። ኢትዮጵያ የራሷን እንጂ የሰው ስለማትፈልግ ኬንያም የእኛን አትፈልግም። ሰላም የምንኖረው ከኬንያ ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች አሜሪካና ሱዳን ናቸው። ሱዳን አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ብትሆንም። በብዙ መልኩ ያስጠቃችን ሱዳን ናት። ጥገኝነት ሰጥታ ስታስወጋን የነበረች ሱዳን ናት። የአሁኑ ጥሩ ይመስልኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያያዝ ብልህነት ነው፤ ይህ በጣም ጥሩ ነው።

ከጎረቤት ውጭ ደግሞ እንደ ግብፅ ያሉ ከሩቅ የሚነሱ ጠላቶች አሉን። ግብጽ አንድም ጊዜ ለኢትዮጵያ ተኝታ አታውቅም። ስለዚህ አገራችን በጣም መጠናከር አለባት። ኃይላችንን በስፋት ማደራጀት አለብን። ሕዝቡ ጠላቱን በትክክል ማወቅ አለበት። አንድ ነገር በመጣ ቁጥር 'ሆ ሆ' ማለቱን ያቁም። ልቦናውን ወደ እግዚአብሄር ይመልስ። የእርስ በእርስ የምናደርገውን ሰዎች ለአገዛዛቸው እንዲመች የነዙትን ፖለቲካ ይዘን እርስ በእርስ አንበጣበጥ። እኔ አባቴና እናቴ ሐረር ነው የተወለዱት። እኔም ሐረር ነው የተወለድኩት። አፌን የፈታሁት በአማርኛና ኦሮምኛ ነው። ከዚያ ሂድ ብባል የት እሄዳለሁ? አዲስ አበባ የመጣሁትም በሥራ አጋጣሚ እንጂ፤ ዛሬም የምወደው ሀገሬ ሐረር ነው። ስለዚህ ለሥልጣን ሲሉ ወያኔዎች ያበጁልንን እንተው።

ወያኔ ለስልጣን ብቻ ሳይሆን ከአማራው መሬት ለመዝረፍ፤ አማራውን የሌለ ታሪክ እየፈጠሩ ማስጠላትና ወገን እንዳያገኝ በማለት ነው ዘመቻ ያደረኩት። እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላየሁት አገር የለም። ደበሎ ለብሶ ከብት የሚጠብቅ የአማራ ልጅ ነው። እግሩ ጫማ የለውም። የሚለብሰው ቁምጣ ነው። ሴቶቹ ጸጉራቸውን ተላጭተው ነው የሚኖሩት። ሴቶቹ ውበታቸው ጸጉራቸው አይደል አንዴለምን አያሳድጉምከችግር የተነሳ ነው። አሁን ኦሮሞው ነቅቷል። አማራው ወንድሙ መሆኑን፣ አብሮ የታገለ ይችን አገር የመሰረተ መሆኑን አውቋል። አገራችን ለእኛ ከበቂም በላይ ናት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም