ቀጥታ፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝብን የሚጠቅም የረጅም ጊዜ ሂደት ነው -- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ህዳር 26/2013 (ኢዜአ) የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝብን የሚጠቅም የረጅም ጊዜ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ፓርቲው በረቂቅ ፖሊሲ ጉዳዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

ረቂቅ ፖሊሲው በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ፣ በአካባቢ ጥበቃና በማኅበራዊ ከለላ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በአጭር ጊዜና በውክቢያ አይከናወንም።

ይልቁንም ግንባታው ሕዝብን የሚጠቅምና ጊዜ የሚጠይቅ ሂደት ነው ብለዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፓርቲው "የሃሳብ ገበያ"ውን በፖሊሲ ሰነድ በማንሸራሸር የሚከራከሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ አውራ፣ ትልቅ አልያም እናት ፓርቲ የሚባል እንዲኖር እንደማይፈቅዱ የገለጹት ሊቀመንበሩ ዜጎች አማራጭ እንዲያገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች "የሃሳብ ገበያ" መፍጠር አለባቸው ብለዋል።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ችግሮች የሚያቃልል ፖሊሲ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ያነሱት ደግሞ የፓርቲው የፖሊሲ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ አማን ይሁን ናቸው።

ረቂቅ ፖሊሲው ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በመለየት፣ በመቀመርና በማደራጀት ችግሮችን በሚፈታና በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ መቀረፁን አስረድተዋል።

ፓርቲው በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች አገራዊ ጎዳዮች ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑም ተነግሯል።

ፓርቲዎች ወደ ምርጫ ከመቅረባቸው በፊት የተደራጀ ሃሳብ በማቅረብና የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማካሄድ ለሕዝብ አማራጮችን እንዲያቀርቡም በመድረኩ አስተያየት ተሰንዝሯል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ግምገማና ውይይት በማካሄድ ግብዓቶች እንደሚሰባሰቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም