ቀጥታ፡

የኢትዮ - ጂቡቲ የባቡር መስመር መሰረተ ልማትን ከጉዳት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ተጠየቀ

አዳማ ህዳር 26/2013 (ኢዜአ) በኢትዮ - ጂቡቲ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመከላከል ሀብቱን ለመጠበቅ የህብረተሰቡ ድጋፍና እገዛ ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በባቡር መስመሩ እየደረሰ ላለው ጉዳት ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ  ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የጸጥታ አካላት ጋር  ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

በዚህ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ  ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ  የባቡር መስመር  መሰረተ ልማት ላይ በሚደርሰው ስርቆትና ሌላም ጉዳት ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እየተጫወተ አይደለም ብለዋል።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው የባቡሩን መስመር ደህንነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት  የሚያስችል  የመፍትሄ ለማስቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በባቡር መስመሩ ያለውን የመሰረተ ልማት ከስርቆት በመከላከል ደህንነቱ እንዲጠበቅ አጥፊዎች አጋልጠው ለህግ በማቅረብ ጭምር ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመስመሩ ያለው  ሁሉንም አካባቢ  ማጠር  ከአቅም አንፃር ባይቻልም ስጋት ያለበት 60 ኪሎ ሜትር መታጠሩን ጠቁመዋል።

ሆኖም  አጥሩን ማፍረስ፣ ሾልኮ መግባትና እንስሳትን ሃዲዱ  ላይ መንዳት ለባቡር  ትራንስፖርቱ እንቅፋት መሆኑንም  አስረድተዋል።

የባቡር ትራንስፖርቱ በሚደርስበት ጉዳት አገልግሎቱ እየተስተጓጎለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ  ጽሑፍ ያቀረቡት  በኮርፖሬሽኑ  የባቡር ደህንነት  ትራንስፖርት  ዘርፍ  ሃላፊ ኢንጅነር ጥላሁን ተረፈ ናቸው።

የባቡሩ ትራንስፖርት የሀገሪቱን ወጪና  ገቢ ንግድ 25 በመቶ የማጓጓዝ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ማዳበሪያ፣ስንዴ፣ብረታ ብረትና ሌሎች ጭነቶችን ጨምሮ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ462ሺህ ቶን በላይ ማጓጓዙን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳት የፍጥነት  ጣሪያውን  ከ80 ኪሎሜትር ወደ 50 ዝቅ ከማድረግ ባለፈ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚፈጀውን ጉዞ ከ12 ሰዓት ወደ 18 ሰዓት ከፍ እንዳደረገው አመላክተዋል።

በዚህም ሴክተሩ በተለይ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ኮርፖሬሽኑ  ከ114  ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት ኢንጅነር ጥላሁን ጠቅሰዋል።

በባቡር መስመሩ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከሰበታ፣ ሉሜ፣ አዳማ፣ ቦሶት፣ ፈንታሌ፣ ሚኤሶ፣ ቦርዶዴ እስከ ደወሌ ድረስ ባሉት መስመሮች እንደሚብስ አመልክተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር  ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ በበኩላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ስለ ባቡር ትራንስፖርት ሀገራዊ ጠቃሜታ ያለው ግንዛቤ የተሟላ ባለመሆኑ በሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለማቃለል በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች  ግንዛቤ  ከማስጨበጥ  ጀምሮ ደህንነቱን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችና የጸጥታ አካላት የባቡር መስመር ደህንነቱን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ  ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን እንደሚጥሩ ተናገረዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ የባበር መስመሩ በሚያልፍባቸው የኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች ከሚገኙ አካባቢዎች የተወጣጡ  አባ ገዳዎች፣ ዑጋዞች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎችም የጸጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም