የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሀዋሳ ህዳር 26 / 2013 (ኢዜአ) የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የወጣቶችን አቅም በመጠቀም ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የሲዳማ ክልል ሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ 14 ኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ቀንን አስመልክቶ በወጣቶች ሀገራዊ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ የውይይት አካሂዷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በመድረኩ እንደተናገሩት ወጣቶች ያልተሳተፉበት የሀገር ግንባታ ሊረጋገጥ አይችልም።
ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቢሮው የክልሉ ወጣቶች በኢኮኖሚው፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የክልሉን ሠላም ለማረጋገጥ የወጣቱ ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህወሃት ጁንታ በሀገር መከላከያ ላይ የፈጸመው ጥቃት ተከትሎ መንግስት የሚወስደውን ሕግን የማስከበር ዘመቻ የክልሉ ወጣቶች ደም በመለገስ ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት በተግባር ማሳየታቸውን ጠቁመው በዚህም አምስት ሺህ 578 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አውስተዋል።
ወጣቶች በትክክለኛው መንገድ ከተመሩ በሀገር ግንባታና ብልፅግና ጉዞ ውስጥ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይም አቅማቸውን በመጠቀም ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የቢሮው የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አለሙ በበኩላቸው አምባገነንነት በተስተዋለባቸው ያለፉት 27 ዓመታት የወጣቱ ተሳትፎ ከሀሰት ሪፖርት የዘለለ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት በሀገር ግንባታ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ የአፍራሽ ተልዕኮ ሰለባ የሚሆኑ ወጣቶች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ አክሊሉ ሁሉም ወጣት በሀገር ግንባታ ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ በእኩልነት ማሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት ብቻ ከ103 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረበው ወጣት አትክልት አጥናፉ በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የህዝብ ቁጥርን የሚይዘው ወጣቱ እንደሆነ ጠቅሶ ይህንን ኃይል ያላሳተፈ ፖሊሲም ሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስኬታማ ሊሆን አይችልም ብሏል፡፡
የወጣቱን አቅም በመጠቀም በሀገር ግንባታ ውስጥ የራሱን አሻራ እንዲያኖር በትክክለኛው መንገድ የሚሳተፍበትን ተቋማዊ መዋቅር መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
ወጣት ምንተስኖት መኩሪያ በበኩሉ አሁን ላይ እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ በመጠቀም ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትግል ማድረግ ይጠበቅብናል ብሏል፡፡
በተለይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸ ጠቁሟል።
በመድረኩ ከክልሉ የሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ወጣቶች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡