በካማሺ ዞን አጋሎሜጢ ወረዳ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር መቆጣጠር ተቻለ

124
አሶሳ ሐምሌ 12/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን አጋሎሜጢ ወረዳ ተከስቶ የነበረ የፀጥታ ችግር በፌዴራልና በክልሉ የጸጥታ አካላት በማሳተፍ ወደ መረጋጋት መመለሱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀጋዬ ተሰማ እንደገለጹት ሀምሌ 9/2010 አንድ የክልሉ የጸጥታ አባል ቀብር ከተፈጸመ በኋላ በተወሰኑ ወጣቶች አነሳሽነት በአካባቢው አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር። ይሔንን አለመረጋጋት ወደ ዋና ከተማዋ ለማዛመት የተደረገው ጥረት የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ህብረተሰቡን በማወያየት መክሸፉን ገልጸዋል፡፡ “በግጭቱም የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና እየተረዱ ይገኛሉ'' ብለዋል። “ግጭቱን ያነሳሱት ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የዘረፋ ተግባር ለመፈፀም ፍላጎት ያላቸው አካላት መሆናቸው ተለይቷል'' ብለዋል ። በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሌሎች አካላትን አጣርቶ የመያዙ ስራ ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በዞኑ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከክልሉ በተጨማሪ የፌዴራል ፀጥታ አካላት የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። “ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ከማህበረሰቡ ጋር በመወያየት የአካባቢው የቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም