የህወሃት ጁንታ ሴራን ያከሸፈ ዲፕሎማሲ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ጁንታ ሴራን ያከሸፈ ዲፕሎማሲ
አብዱራህማን ናስር /ኢዜአ/
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረችና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ከሆኑ ቀደምት አገራት መካከል አንዷ ነች። ከአፍሪካ ብቸኛዋ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ዓለም አቀፍ ግንኙነትን በመፍጠርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በማክበር የምትታወቅ ነች። የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስትታት ድርጅት ሲመሰረቱ የኢትዮጵያ ሚና የጎላ ከመሆኑም በላይ ቀዳሚ ሚና በመጫወት ለበርካታ ሀገራት ምሳሌ በመሆን ትጠቀሳለች፡፡
ኢትዮጵያ ካላት ረጅም ዕድሜ አኳያ በዲፕሎማሲው መስክ ልምድ ያዳበረች አገር ነች። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ የተመድ እና የአፍሪካ ህብረት መስራች ለሆነችው ኢትዮጵያ ስለዲፕሎማሲና ማልቲላተራሊዝም አይነገራትም ብለዋል። ኢትዮጵያ በሰላምና በድርድር የምትታወቅ መሆኗን በመጠቆም በኮሪያና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሰላም ማስከበር ተልእኮ ድጋፍ ማድረጓንም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ለመሆን የሀገሪቱን እውነታ መረዳት እንደሚገባ አስምረው ተናግረዋል። ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ እንደመሆኗ ቀጠናው ትርምስ የማያጣው በመሆኑና በተለይ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ባላት አስተዋጽኦ የበርካታ አገራት ትኩረት ትስባለች። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ማናቸው አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ክስተቶች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅርበት ይከታተለዋል።
የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ የሰነዘረው ጥቃት የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። ድርጊቱ በትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ስለመፈጸሙ የህወሃት ቡድን አባል አቶ ሴኩ ቱሬ ጌታቸው በድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ቀርበው “የ45 ደቂቃ መብረቃዊ እርምጃ” መካሄዱን በይፋ ተናግረዋል። የጥቃቱ ዋነኛ ዓላማ መከላከያን በመበታተን ሀገሪቱን ለብጥብጥና ለእርስ በርስ ግጭት ማጋለጥ ነበር። ይህም ቡድኑ በአገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የነበረውን የበላይነት መልሶ ለማግኘት ካለው ምኞት የመነጨ ነው።
የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የከፈተው ጦርነት ህግን የጣሰና የአገር ሉአላዊነትን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ መንግስት ህግን ለማስከበር ፈጣን እርምጃ ወስዷል። ‘ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል’ እንደሚባለው የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን የአገርን ሉአላዊነት በሚጠብቀው መከላከያ ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙ ሳያንሰው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተዛባ መንገድ እንዲገነዘበው ለማድረግ ከፍተኛ ጫጫታ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ይህንንም ለማድረግ ከ27 ዓመታት በላይ የሀገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በቁጥጥሩ በነበረበት ወቅት በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በተለያዩ የዓለም አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተልእኮውን እንዲያስፈጽሙ ባስቀመጣቸው አካላት በኩል የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን አሰራጭቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ የህወሃት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመው በእብሪትና በትእቢት ተወጥሮ መሆኑን ጠቁመው አስቀድሞም ቡድኑ “እኛ የምንለውን መንግስት ካልፈጸመ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካን እንበጠብጣለን” ሲሉ በይፋ በመድረኮቻቸው ሲናገሩ እንደበር ገልጸዋል። ይህንንም መልእክት በዲፕሎማቶች በኩል ሲያስተላልፉ እንደነበር አመልክተው ዲፕሎማቶቹም እነዚህን ከነካችኋቸው ቀጠናው ይታመሳል በማለት ለማግባባት ሲሞክሩ እንደነበር ገልጸዋል። የጁንታው ቡድን ቀደም ብሎ ገንዘብ በመርጨት ያሰማራቸው አካላት በየአገራቱ ሎቢ የማድረግ ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል። በዚህም በዲፕሎማሲው መስክ፣ በሚዲያው እንዲሁም በሁሉም መስክ ውጊያ ተከፍቶ እንደነበር ጠቅሰው ብዙዎቹ ወደ ድርድር እንድንገባ ግፊት ሲያደርጉ ነበር ብለዋል።
የክልሉን ሚዲያ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ባሰማራቸው ሰራዊቶቹ ችግሩ በመላው የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተ ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እንዲኖረው ለማስመሰል ብዙ የፈጠራ ወሬዎችን ፈብርኳል። ቡድኑ ያሰማራቸው አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተንታኞችም የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሱን፣ ሀገሪቱ ወደ መበታተን ጫፍ ላይ መድረሷን በመጥቀስ ከነባራዊ እውነታው ያፈነገጠ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ሞክረዋል። አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ መንገድ ተከትለው የተዛባ መረጃ አሰራጭተዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በቅርቡ ለአንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊነት የጎደለው መረጃ እንደሚያሰራጩ በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ይታወሳል። ለምሳሌ ሮይተርስ፤ ቢቢሲ (አማርኛና እንግሊዝኛ ፕሮግራሞች)፤ የጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም፤ እና አልጀዚራ (እንግሊዝኛ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ውጊያው የእርስበርስ ጦርነት እንደሆነ አስመስሎ የማቅረብ እንዲሁም ከክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊነት ጋር በማያያዝ፣ ሊፈጠር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ በተጋነነ መልኩ በመሳል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር የማድረግ አዝማሚያ እንደነበራቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
የህወሃት ቡድን በአገር ውስጥ ያለው ሁኔታ አልሳካ ሲለው ግጭቱ ቀጠናዊ ይዘት እንዳለው ለማስመሰል “በርካታ የውጭ አገራት በውጊያው ተሳታፊ በመሆን እያጠቁን ነው” በማለት ኤርትራ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬት እንዲሁም ሶማሌያ በውጊያው እንደተሳተፉ ለማስመሰል ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቶ ነበር። ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ከፍተኛ ድብደባ ፈፅመዋል፤ በባድመ በኩል በመግባት ጦርነት ከፍተዋል ሲሉ ተደምጠዋል። አያይዘውም የኤርትራ መንግሥት በጦርነቱ ተሳታፊ በመሆን ጦርነቱን ወደተለየ ምዕራፍ አሸጋግሮታል ብለዋል። የሀሰት ፎቶዎችን በመለጠፍ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ያሰራጨው መረጃም እውነታው እየተጋለጠበት ስለተቸገረ ብዙ ሊያስኬደው አልቻለም።
ጉዳዩን ቀጠናዊ ለማድረግ በማሰብ ጽንፈኛው ቡድን ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ በተደጋጋሚ ሮኬቶችን አስወንጭፏል። ይሁን እንጂ ኤርትራ አጸፋዊ ምላሽ ባለመስጠት ሴራው ሊከሽፍ ችሏል። የቡድኑ ድርጊትም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ውግዘትን አስከትሏል። ከኤርትራ ጋር ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመረው አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የተፈጠረው ሰላም ለህወሃት ቡድን መፈናፈኛ ሲያሳጣት ለኢትዮጵያ መንግስት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።
በመከላከያ ሰራዊት ላይ በተፈጸመው ጥቃት አምልጠው ወደ ኤርትራ የገቡት አባላት አልብሰው አብልተው ሸኝተዋቸዋል። ሌተናል ጄኔራል ባጫ ለመገናኛ ብዙሃን ስለሁኔታው እንዳብራሩት የሠራዊቱን አባላት ከመግደል ባሻገር ያፈኗቸውን የደንብ ልብሳቸውን አስወልቀው ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ አድርገዋል።
የሚገርመው ግን የኤርትራ ሠራዊት አባላት የራሳቸውን ልብስ አውልቀው እርቃናቸውን ሸፍነውላቸዋል፤ ወገን ከሚሉት አካል ጥቃት ሲደርስባቸው የኤርትራ ሠራዊት ግን መጠጊያ ሆኗቸዋል። በተመሳሳይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የተነሳ በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች።
የህወሃት ቡድን ባሰራጫቸው የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የአንዳንድ አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ውጊያው ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊያመራ ይችላል በማለት እንዲሁም ቀጠናዊ ይዘት አለው የሚል የተዛባ መረዳት በመያዝ በድርድርና በውይይት እንዲፈታ ግፊት ማድረግ ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተከታታይ እውነታውን ለማስረዳት በተሰራው ስራ ብዙዎቹ ትክክለኛውን ግንዛቤ ሊይዙ ችለዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል የተወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ለጎረቤት አገራትና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የሀገራት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ በመስጠት ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡ በመቀጠል የተለያዩ ሀገራት መሪዎችንና ድርጅቶችን አመራሮች በስልክ ጭምር በማነጋገር ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የኢፌዴሪ መንግስት የሀገሪቱን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ በቂ መረጃ ላልነበራቸው ሀገራትና መሪዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማብራሪያ ለመስጠትና ቀጣይ በሚኖሩ የሁለትዮሽና ባለብዙ ግንኙነቶችና የትብብር ስራዎች ላይ ለመምከር በተለያዩ ሀገራት ካሉ ኤምባሲዎችና ቆንጽላ ጽ/ቤቶች በተጨማሪ በከፍተኛ ባለስልጣናት የተመራ ልዑካንን በማሰማራት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል። እንደ ኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ወደ ተለያዩ አገራት የሄዱ ልዑካን ቡድኖች፣ አምባሳደሮችና ቆንጽላ ጀነራሎች በተሰማሩባቸው ሀገራት መንግስታትና ተቋማት በቂ ማብራሪያና ገለጻ በማድረግ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል።
ወደተለያዩ አገራት ከተጓዙት ልዑካን መካከል በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራው ይገኝበታል። ፕሬዝዳንቷ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና ህግን የማስከበር ዘመቻ ዓላማ አስገንዝበዋል። በተመሳሳይ በጅቡቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ተገኝተው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በወቅቱም የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በጎረቤት አገራት ማለትም ለደቡብ ሱዳን እና ለሶማሌያ መሪዎች ማብራሪያ በመስጠት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው ልኡክ በደቡብ ሱዳን ተገኝቶ ማብራሪያ ሰጥቷል። የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር “ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የቆመችው ኢትዮጵያ በሰራችው ስራ ነው በመሆኑም የደቡብ ሱዳን ህዝብ እና መንግስት ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ይቆማሉ” በማለት መንግስት እየወሰደ ላለው ህግን የማስከበር እርምጃ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተለያዩ አገራት ባደረጓቸው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እውነታውን አስገንዝበዋል። በውይይቱ ወቅትም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲደናቀፍ እንደማይፈልጉና ለለውጡ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ምርመራ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች ኢትዮጵያ ለህብረቱ ስትራቴጂያዊ አጋር እንደሆነች በመግለጽ መንግሥት በጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃ የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል።
የሩሲያ የወዳጅነት ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት በነበረው ውይይት ላይ ሩሲያ በማንኛውም ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ አሳውቃለች።
በተለያዩ አገራትና ተቋማት ኢትዮጵያን የወከሉ ዲፕሎማቶችም በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ለተቋማቱና ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ገለጻ አድርገዋል። በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህግን የማስከበር ዘመቻው አስመልክተው ዝርዝር ማብራሪያ በማቅረብ እውነታውን አስገንዝበዋል። በሱዳን፣ በታንዛንያ፣ በኬንያ በአልጄሪያ፣ በግብጽ፣ በሩሲያ፣ በቤልጂየም፣ በጃፓንና በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ቆንጽላ ጀነራሎች በየሀገራቱ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የጦር መኮንኖችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጉዳዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያው ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮችና የተቋማት ተወካዮች ጥሩ ግንዛቤ መያዛቸውን እንዲሁም ሀገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በተለያዩ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በመጠቀም እውነታውን ለማስገንዘብ በተሰራው ስራ የሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮቻቸው እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ችግሩ የውስጥ እንጂ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደሌለው መገንዘብ ችለዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ አጋርነት ግምት ውስጥ በማስገባት የሃገሪቱን ሰላም የሚፈትኑ የውስጥ ጉዳዮች እንደ ወዳጅ ሃገር የሚያሳስባቸው መሆኑን በመግለጽ፤ መንግሥት በጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ለንፁሃን ዜጎች ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግን የማስከበርና የአገርን ህልውና የመታደግ እርምጃ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንዲሁም ችግሩ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ለማስመሰል ያገኙትን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመዋል። በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ አጋሮቹንና ሸሪኮቹን አሰማርቷል። ይሁን እንጂ በሂደት ሴራው እየተጋለጠ ከመሄዱም ባሻገር በፈጸመው የክህደት ተግባር በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት ምእራፍ ላይ ደርሰል።
በአንጻሩ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ክልል የተወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ዓላማ አስመልክቶ በተሰራው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ግንዛቤው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሊመጣ ችሏል። ከየትኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ ምሁራንና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ህግን የማስከበር ዘመቻው ዓላማና ግብ ተንትነው አስረድተዋል። በዚህም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ በመንግስት ላይ ያልተገባ ጫና እንዳይፈጥር ከማድረጉም ባሻገር የጁንታው ህወሃት ቡድን ዕቅድ እንዲመክን በማድረጉ በኩል የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። የጁንታው ድብቅ ትርምስ የመፍጠር አጀንዳና ፍላጎትም ሳይሳካ ቀርቷል።