ቀጥታ፡

ምርጫው ግልጽና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የተጀመሩ ነጻ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው--ፓርቲዎች

አዲስ አበባ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የተጀመሩ ነጻ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከትላንት በስቲያ ‘’የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ 2013 ቁልፍ የሽግግር ምዕራፍ’’ በሚል ሃሳብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎች እንዳሉት ፓርቲዎች በነጻነት ሃሳባቸውን እንዲያጸባርቁና የተሻለ ሃሳብ ይዘው እንዲወጡ ችግሮቻቸው ሊፈታ ይገባል።

ለዚህም የሚደረጉ ግልጽ ውይይቶች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ለቀጣይ ምርጫ ብቁ ሆኖ ለመቅረብ ወሳኝ ሚና አላቸው ይላሉ።

በተለይ ፓርቲዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የያዙትን አጀንዳ ለማስተዋወቅ አስቀድሞ የሚገጥማቸውን ችግር በውይይት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ ሊቀመንበር፤ አቶ የሺዋስ አሰፋ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው።

በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት መንግስት ምርጫው ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን ያለውን ግልጽ አቋም መረዳት ችለናል ብለዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ፓርቲዎች ግልጽ መረጃ እንዲያገኙ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የፓርቲ አመራሮች የራሳቸውን ሃሳብና በቀጣይ መፈታት ስለሚገባቸው ጉዳዮች በግልጽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየት ችለዋል ብለዋል።

መንግስትና ህዝብም ፓርቲዎች እንዲጎለብቱ ድጋፍ ማድረግና ችግሮቻቸውን በቅርበት መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ውይይቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ባለፉት ጊዜያት አገራዊ ምርጫዎች ላይ የታዩ ህጋዊ ያልሆኑ አካሄዶች እንዲቀረፉ ያስችላል ብለዋል። 

"ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎች በጉልበት የተገኙ ስልጣን ማስቀጠያዎች እንጂ የተሻለ ፓርቲ አሸንፎ እንዲወጣ የተሰራ አልነበረም፤ ዘንድሮ ይህን አንጠብቅም" ብለዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዳሉት በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ ቀጣይነታቸው መረጋገጥ አለበት።
የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በፓርቲዎች መብዛት፤ እንዲሁም የሚገጥማቸውን ችግር በንግግር ለመፍታት ውይይቶችና መፍትሄዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

መንግስት በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች የማይደገሙበት ለማድረግ በትኩረት መሰራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም