ቀጥታ፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዳይቀዛቀዝ ለውጭ ባለሃብቶች በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) ለውጭ አገራት ባለሃብቶች የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ማብራሪያና ገለጻ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ። 

ኮሚሽነር ሌሊሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ ለውጭ ባለሀብቶች ስለ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ላይ ይገኛል።

መረጃውን የሚሰጠው ባለሃብቶቹ በወቅታዊው አገራዊ  ጉዳይ በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ በመመርኮዝና በራሱም መንገድ በማሰባሰብ መሆኑን ገልጸዋል።   

መረጃው በትግራይ ከልል ለሚሰሩ ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎችም የአገሪቷ አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች ጭምር ታስቦ እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ይህም ለባለሃብቶቹ መተማመንን እንደፈጠረላቸው ነው ኮሚሽነር ሌሊሴ የገለጹት።

በሌላ በኩል ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ደረጃ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ማሳየቱን ኮሚሽነሯ አስታውሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ /አንክታድ/ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮጳዊያኑ 2020 በአፍሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ኢንቨስትመንት ከ30 እስከ 40 በመቶ  እንደሚቀንስ ማመልከቱን ጠቅሰው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተቀዛቀዘው ኢንቨስትመንት መልሶ እንዲያንሠራራ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያስፋፉ በማበረታታት ላይ መሆኑን ወይዘሪት ሌሊሴ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧን ኮሚሽነር ሌሊሴ አስረድተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም