ጁንታው የዘራውን የብሄር ጥላቻንና ግጭትን በማስቀረት ለሀገሪቱ የብልፅግና መረባረብ ይገባል--የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ጁንታው የዘራውን የብሄር ጥላቻንና ግጭትን በማስቀረት ለሀገሪቱ የብልፅግና መረባረብ ይገባል--የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ
ሀዋሳ ህዳር 25 /2013 (ኢዜአ) ሁሉም ዜጋ ጁንታው የዘራውን የብሄር ጥላቻንና ግጭትን በማስቀረት ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ መሳካት እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ።
በሲዳማ ክልል ምክር ቤት አዘጋጅነት 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ እንዳሉት የህወሓት ጁንታ በሚከተለው ተንኮልና ሴራ የተሞላበት ሥርዓት ህዝቡ ብዙ መከራ አስተናግዷል።
ከህገ መንግስቱ በተቃረነ መልኩ ዜጎች እንዲጋጩ በማድረግ የጁንታው ህወሃት የጥፋት ፍላጎት ለማሳካት ሲሞክር መቆየቱን አውስተዋል።
በተለይ የሲዳማ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ሲያነሳ የነበረው የአደረጃጀት ህገ መንግስታዊ መብት በጁንታው ታፍኖ ትልቅ ኪሳራ ማድረሱን ጠቅሰዋል።
ሆኖም እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን የለውጡ አመራሮች ባሳዩት ቁርጠኝነትና ትጋት የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይ ሁሉም ዜጋ ጁንታው የዘራውን የብሄር ጥላቻንና ግጭትን በማስቀረት ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ መሳካት እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ከነችግሮቹም ቢሆን በማንነታችን ሳንሸማቀቅ በአደባባይ እንድናከብር ያደረገን በዓል ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ሌላኛው የክብር እንግዳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ሰፊው የሲዳማ ህዝብ ሲያነሳው የነበረው በክልል የመደራጀተ ጥያቄው ህገ መንግስታዊ ምላሽ እንዲያገኝ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግፊት በማድረግ አጋርነቱን ማሳየቱን ተናግረዋል።
ዛሬ አህዳዊ ብሎ የለውጡን አመራር ጥላሸት የሚቀባው ጁንታው ህወሃት እራሱ አህዳዊ መሆኑን የሲዳማ ህዝብን የመብት ጥያቄ በማፈን በግልፅ አሳይቷል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ በዓሉን ስናከበር የክልሎችን ህዝብ ለህዝብ ትስስር ባጠናከረ መልኩ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተናል ብለዋል።
ባለፉት ስምንት ቀናት በዓሉ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በፓናል ውይይት፣ለመከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ ፣በፅዳት ዘመቻና በሌሎችም መረሃ ግብሮች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል በሲዳማ የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪ አቶ በቀለ ምትኩ በሰጡት አስተያየት ላለፉት 27 ዓመታት በአመለካከት ልዩነቶች ሳቢያ በሚፈጠሩ ችግሮች ህዝቡ መጎዳቱን ተናግረዋል።
ችግሩ ከለውጡ ወዲህ እየተቃለለ መጥቶ የክልሉ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ በዓሉን በልዩ ደስታ እንዳከበሩት ገልጸዋል።
በዓሉን ስናከብር ከመለያየት ይልቅ ለሰላም በመምከር፣ለሀገራዊ አንድነት እና ለህግ የበላይነት መስፈን በመትጋት ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚና የምዕራብ አርሲ ዞን አባገዳ ነጌሶ ገመቹ ናቸው።
በሀዋሳ ከተማ በተከናወነው የበዓሉ ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ እንደ ሀገር እየተዘዋወረ ያለው የህብረ ብሔራዊ አንድነት ችቦ የኦሮሚያ ክልል ለደቡብ ክልል አስረክቧል።